ጃፓን፣ ሰሜን ኮሪያ፥ እ.ኤ.አ. ከግንቦት 31 እስከ ሰኔ 11 ድረስ፣ የባለስቲክ ሚሳየሎቿን የማስወንጨፍ ሙከራ ለማድረግ ማቀዷን ከገለጸች በኋላ፣ የባለስቲክ ሚሳየል መከላከያዋ በተጠንቀቅ እንዲቆም ዛሬ ሰኞ ትዕዛዝ ሰጥታለች፡፡
በግዛቷ ላይ ስጋት የሚጋርጥን ማንኛውም መሣሪያ፣ መትታ እንደምትጥልም፣ ጃፓን ከወዲሁ አስጠንቃቀለች፡፡
የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሙዬ ኪሻዳ፣ ሰሜን ኮሪያ የምታስወነጭፋቸው ሚሳየሎች በሙሉ፣ እንደ ትንኮሳ ይቆጠራሉ፤ ሲሉ፣ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡
“የባለስቲክ ሚሳየል ቴክኖሎጂዎችን ማስወንጨፍ፣ ሳተላይት እንኳን ቢኾን፣ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔዎችን መጣስ እና የሰዎችን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ከባድ ችግር ነው፤” ሲሉም አክለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ጃፓን ወደ ምድር የቀረቡ የጦር መሣሪያዎችን አውርደው መጣል የሚችሉ የጦር መሣሪያዎችን፣ ወደ ኢኮናዋ ደሴቶች አሠማርታለች፡፡
ባለፈው ወርም እንዲሁ፣ ዒላማዎቻቸውን በሕዋ ላይ ቀድመው መምታት የሚችሉ ሚሳየሎችን የተሸከሙ፣ የባሕር ኃይል ደምሳሽ መሣሪያዎችን፣ ወደ ምሥራቅ ቻይና ባሕር መላኳ ተመልክቷል፡፡
የኑክሌር ጦር መሣሪያ የታጠቀችው ሰሜን ኮሪያ፣ የመጀመሪያዋ የኾነውን ወታደራዊ የስለላ ሳተላይት ሥራ ማጠናቀቋን አስታውቃለች፡፡
የአገሪቱ መሪ ኪም ጆን ኡን፣ ሳተላይቷ የምትመጥቅበትን የመጨረሻ ዝግጅት እንዳጸደቁም ታውቋል፡፡
ተንታኞች እንደገለጹት፣ ሳተላይቱ፥ ድርኖችን ጨምሮ በጦርነት ወቅት ዒላማዎችን በትክክል የመምታትን ዐቅም የሚያሳድግ የስለላ ቴክኖሎጂ ፕሮግራም አካል ነው፡፡
ሰሜን ኮሪያ፣ ባለፉት ቅርብ ወራት፣ ፈሳሽ ያልኾኑ ጠጣር የነዳጅ አማራጮችን(solid-fuel) የሚጠቀሙ፣ አህጉር አቋራጭ የባለስቲክ ሚሳየሎችን ጨምሮ፣ ተከታታይ ሚሳየሎችንና የጦር መሣሪያዎችን መሞከሯ ተመልክቷል፡፡