ዮሺሂዴ ሱጋ አዲሱ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ዛሬ በይፋ ተመርጠዋል።
የጃፓን ፓርላማ የታችኛው ምክር ቤት በከፍተኛ ድምፅ የመረጣቸው የሰባ አንድ ዓመት ሱጋ ሹመታቸውን ደጋግመው እጅ በመንሳት ተቀብለዋል። ሱጋን ገዥው ሊበራል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ፕሬዚዳንቱ አድርጎ የመረጣቸው በመሆኑ ያን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትርነቱ መያዛቸው ያለቀለት ጉዳይ ነበር። ሱጋ ከማናቸውም የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ለበለጠ ዘመን ሃገሪቱን የመሯትን ሽንዞ አቤን ነው የተኩዋቸው።
ለሥምንት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትርነት የቆዩት አቤ በጤና መታወክ ለረጅም ጊዜ የቆየባቸው የአንጀት መቆጣት ምክንያት ባለፈው ወር በድንገት ሥልጣናቸውን መልቀቃቸው ይታወሳል።
ተተኪያቸው ሱጋ በኮቪድ-19 ምክንያት ከደረሰባት የኢኮኖሚ መዳከም እያገገመች ያለችውን ሃገር ነው የተረከቡት። በወረርሽኙ ምክንያትም በከፍተኛ ጉጉት ሲጠበቅ የቆየውን የቶኪዮ ኦሎምፒክ እኤአ 2021 እንድታስተላላፍ ተገዳለች። በእድሜ የገፉ ዜጎችዋ ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ መምጣቱም ሌላው ፈተና ነው።
አዲስ ተመራጩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዮሽሂዴ ሱጋ “አቤኖሚክስ” የሚል ስያሜ የተሰጠውን የሽንዞ አቤን የኢኮኖሚ መርሃ ግብር እንደሚያስቀጥሉ ቃል ገብተዋል።
ሃገራቸው ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ያላትን የጸና ግንኙነት መጠበቅን የመሳሰሉትን የአቤን የዲፕሎማሲ ርምጃዎችም እንደሚከተሉ አስታውቀዋል።