በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኮቪድ ክትባት በጃፓን


ጃፓን ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የቆየውን የኮቪድ-19 ክትባት መርሃ ግብሩዋን በዛሬ ዕለት ጀምራለች።

የመጀመሪያውን በፋይዘር እና በባዮንቴክ ኩባኒያ በትብብር የተሰራውን ክትባት የተቀበለው በቶኪዮ የሚገኝ ሆስፒታል ዛሬ የመጀመሪያውን ሰው ከትቧል።

በቀዳሚነት ቁጥራቸው ወደ አርባ ሽህ የሚጠጋ ዶክተሮች እና ነርሶች ይከተባሉ፣ ከዚያም እስከመጪው መጋቢት በሚኖረው ጊዜ ውስጥ ሦስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን የህክምና ሰራተኞችን ለመክተብ ዕቅድ ተይዟል፤ በማስከተል ደግሞ ዕድሜያቸውን ስድሳ አምስት ዓመት የሞላቸው ሠላሳ ስድስት ሚሊዮን ዜጎች ይከተባሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ደቡብ አፍሪካ በዩናይትድ ስቴትሱ የመድሃኒት ኩባኒያ በጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የተሰራው ቁጥሩ ወደ ሰማኒያ ሽህ የሚጠጋ ክትባት ትናንት በጆሃንስበርግ ከተማ ተቀብላለች።

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በሚቀጥለው ሳምንት ክትባቶቹን ለጤና ሰራተኞች በመስጠት ክትትል እንደሚያደርግ አስታውቋል። የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ እኔም ክትባቱን እወስዳለሁ ማለታቸው ተጠቅሷል። በቀጣዮቹ ሳምንታት ውስጥ በአጠቃላይ አምስት መቶ ሽህ ክትባቶች እንደሚላክላት ነው የተገለጸው።

ከዚህም ሌላ በፋይዘር እና ባዮንቴክ ኩባኒያ በህብረት የሰሩ ሃያ ሚሊዮን ክትባቶች እንደምታገኝ ተመልክቷል።

ቀደም ብላ ደቡብ አፍሪካ በአስትራ ዜኔካ እና ኦክስፈርድ ዩኒቨርስቲ የተሰራውን የኮቪድ ክትባት ገዝታ እንደነበር ሲታወስ በሀገርዋ የተከሰተው የተለየ የኮሮናቫይረስ ዓይነት እምብዛም የማይከላከል ነው የሚል ጥናት ከወጣ በኋላ ክትባቱን ጥቅም ላይ ላለመዋል ወስናለች።

የደቡብ አፍሪካ የጤና ሚኒስትር ክትባቶቹን ለተለያዩ የአፍሪካ ሃገሮች እንዲያከፋፍል ለአፍሪካ ህብረት እንሰጣለን ብለዋል።

XS
SM
MD
LG