በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጣሊያን ከሊባኖስ፣ አይቮሪ ኮስት እና ኢትዮጵያ ሠራተኞችን ልትመለምል ነው


ፎቶ ፋይል፦ የጣሊያን ካርታ
ፎቶ ፋይል፦ የጣሊያን ካርታ

ጣሊያን ከሊባኖስ፣ አይቮሪ ኮስት እና ኢትዮጵያ 300 ሰዎችን በሠራተኝነት ልትቀበል መሆኑን አስታውቃለች። 'ሳንትኤጂዲዮ' ማኅበረሰብ በተሰኘ የካቶሊክ በጎ አድራጎት እና የመብት ተሟጋች ተቋም በሚመራ የሙከራ ፕሮጀክት ስር የሚመለመሉት ሠራተኞች፣ በስደተኝነት እንደማይመዘገቡም ተገልጿል።

ሳንቴጂዲዮ ፕሮጀክቱን ለመጀመር 'የሥራ ኮሪደር' የተሰኘ ስምምነት አርብ እለት ከጣሊያን የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ጋር የተፈራረመ ሲሆን፣ ስምምነቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ቀኝ ዘመም መንግስት በህገወጥ ስደት ላይ የሚከተለውን ጥብቅ መንገድ ለማመጣጠን፣ አንዳንድ ህጋዊ መንገዶችን ለመዘርጋት የገባውን ቃል የተከተለ ነው።

ጣሊያን በዓለም ላይ በእድሜያቸው የገፉ ሰዎች በብዛት የሚገኙባት እና በጣም በፍጥነት እየቀነሰ ያለ የህዝብ ብዛት ያላት ሀገር ናት። በዚህም ምክንያት እንደ ፋብሪካ ሥራ፣ እንግዳ ተቀባይነት እና የቤት ውስጥ እንክብካቤ ለመሳሰሉ ዝቅተኛ ክፍያ የሚከፈላቸው የጉልበት ሥራዎች ከፍተኛ የሠራተኛ እጥረት አለባት። የንግድ ተቋማትም ከአውሮፓ ህብረት ውጪ ካሉ ደሃ ሀገራት በአንፃራዊ ርካሽ የሰው ኃይል ለመመልመል ሙከራ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

የሳንቴጂዲዮ ሠራተኞች ስደተኞችን ከትውልድ ሀገራቸው በመመልመል የሚቀጥሯቸው ሲሆን፣ ወደ ጣሊያን ከመሄዳቸው በፊት ጣሊያንኛ ቋንቋ እና ለሚቀጠሩበት ሥራ የሚሆን የሞያ ሥልጠና እንደሚሰጣቸው የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ገልጿል።

ጣሊያን ባለፈው ዓመት ከሰሜን አፍሪካ በባህር የመጡ ወደ 158,000 የሚጠጉ ህገወጥ ስደተኞችን የመዘገበች ሲሆን በዚህ አመት ብቻ ከ16 ሺህ በላይ መመዝገባቸውን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

የሜሎኒ አስተዳደር እ.አ.አ ከ2023 እስከ 2025 የአውሮፓ ህብረት ዜግነት ለሌላቸው ሰዎች የሚሰጠውን የሥራ ቪዛ ቁጥር ወደ 452 ሺህ አሳድጓል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG