በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጣሊያን የኢራኑን አምባሳደር ጠርታ ጋዜጠኛዋ እንድትፈታ ጠየቀች


ዘጋቢ ሴሲሊያ ሳላ
ዘጋቢ ሴሲሊያ ሳላ

የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቴህራን ውስጥ በጋዜጠኝነት ቪዛ ፈቃድ ስትሠራ የነበረችው እና እኤአ ታኅሣሥ 19 ቀን የታሰረችውን ዘጋቢ ሴሲሊያ ሳላ በአስቸኳይ እንድትፈታ ዛሬ ሐሙስ የኢራን አምባሳደርን ጠርቶ ጠይቋል።

የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው የሳላ መታሰር እንዳሳሰበው በመግለጽ ሰብአዊ አያያዝ እና የሰብአዊ መብቶቿ መከበር ላይ አፅንዖት ሰጥቷል።

የጣሊያን ብዙኅን መገናኛ እንደዘገቡት፣ "ሳላ ሌሊትና ቀን የደበዘዘ መብራት ባለው ቀዝቃዛ ክፍል ውስጥ ከሌሎች እስረኞች ተለይታ ለብቻዋ ታስራለች። የዐይን መነጽሯን የተቀማች ሲሆን፣ ከውጭ ዓለም ጋራ ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳይኖራት ተደርጓል" ብለዋል፡፡

የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና ጸሐፊ ሪካርዶ ጉዋሪሊያ ቴህራን የሚገኙ የሀገራቸው ኤምባሲ ሠራተኞች፣ ሳላን እንዲጎበኙ እና "እስካሁን የተከለከለቻቸውን የመገልገያ ዕቃዎች" እንዲያስገቡላት እንዲፈቀድ ጠይቀዋል።

የኢራን የዜና ወኪል ኢርና ባለፈው ሰኞ እንደዘገበው ሳላ "የኢስላማዊ ሪፐብሊክ ሕግን በመጣስ" በቁጥጥር ሥር ውላለች” ከማለቱ በቀር ተጨማሪ መረጃ አልሰጠም።

ጋዜጠኛዋ በቁጥጥር ስር የዋለችው ኢራናዊው ነጋዴ መሐመድ አቤዲኒ፣ በሚላን፣ ማልፔንሳ አውሮፕላን ማረፊያ ከታሰረ ከሦስት ቀን በኋላ ነው፡፡

አቤዲኒ የታሰረው ዋሽንግተን እ ኤ አ በ2023 ዩርዳኖስ ውስጥ የነበሩ ሦስት አሜሪካውያን ለተገደሉበት የድሮን ጥቃት ለድሮኑ መሥሪያ የሚውሉ እቃዎችን አቅርቧል በሚል የእስር ማዘዣ ስላወጣችበት ነው፡፡

ኢራን በጥቃቱ እጇ እንደሌለበት ስትገልጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ የኢራን ብዙኅን መገናኛ ጠቅሰው የአቤዲኒ እስር ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ ነው ብለዋል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኢራን የጸጥታ ኃይሎች በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎችን እና ጥምር ዜግነት ያላቸውን ኢራናውያንን ፣ በአብዛኛው በስለላ እና በጸጥታ ወንጀሎች በመክሰስ በቁጥጥር ስር አውለዋል።

የመብት ተሟጋች ድርጅቶች “ኢራን እንደዚህ ዓይነቶቹን እስሮች ከሌሎች ሀገራት ጋራ ለመደራደሪያ ለመጠቀም እየሞከረች ነው” ሲሉ ክስ ያሰሙ ሲኾን ኢራን ይህንን አስተባብላለች።

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በሳላ ጉዳይ ላይ ከውጪ ጉዳይ እና ከፍትህ ሚኒስትሮቻቸው ጋራ ዛሬ ማምሻውን እንደሚመክሩ ጽሕፈት ቤታቸው አስታውቋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG