የጣልያን የባህር ድንበር ጠባቂዎች ከአንድ ሺህ በላይ ፍልሰተኞችን ከሜዲትሬኒያን ባህር ላይ መታደጋቸውንና ሁለት አስከሬኖች ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።
በሁለት የዓሳ ማስገሪያ ጀልባዎች ላይ የተካሄደው የነፍስ ማዳን ሥራ በሲሲሊ አቅራቢያ የተካሄደ መሆኑንና፣ ጀልባዎቹ ከሊቢያ መነሳታቸውን የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል። የድረሱልን ጥሪው ፍልሰተኞች በአደጋ ወቅት እንዲጠቀሙበት ወደተዘጋጀው ስልክ ማክሰኞ ዕለት መደውሉም ታውቋል።
ባለፈው ሣምንት መጨረሻ ሥልጣን የተቆናጠጡት የጣልያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ መሎኒ ማክሰኞ ለመጀመሪያ ግዜ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር፣ ከአፍሪካ የሚነሱ ፍልሰተኞችን ለማስቆም ቃል ገብተዋል።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ የቀኝ አክራሪ መንግስት ሥልጣን በያዘባት ጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት መሎኒ፣ መንግስታቸው ፍልሰተኞችን ከመነሻቸው ለማስቆምና ሕገ-ወጥ ዝውውርን ለመስበር እንደሚፈልግ ተናግረዋል። የመነሻ ምንጭ ከሆነው ሊቢያ የሚደረገውን ጉዞ ለማስቀረት ቃል ገብተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሞሮኮ በበኩሏ 23 ሕገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎችን ባለፈው ሰኔ ፍልሰተኞች ባለቁበት ድንበር ላይ መያዟን አስታውቃለች። ከተያዙት ውስጥ ሞሮኮያውያንና፣ አራት ከሰሃራ ግርጌ ካሉ ሃገሮች የመጡ እንደሚገኙበት ታውቋል።
ዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት ማክሰኞ ባወጣው ሪፖርት እአአ ከ2014 ወዲህ 29ሺህ ፍልሰተኞች ሲሞቱ፣ ከዚህ ውስጥ 5 ሺዎቹ ህይወታቸውን ያጡት ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ መሆኑን አመልክቷል።