ዋሽንግተን ዲሲ —
በስድስት ጀልባዎች ተሳፍረው ከቱኒዥያ እና ከሊቢያ የተጓዙ ስደተኞች ትናንት ዕሁድ ጣልያኗ ላምፔዱሳ ደሴት መድረሳቸው ተገለጸ።
ሁለቱ ጀልባዎች ከሊቢያ አራቱ ደግሞ ከቱኒዥያ የተነሱ መሆናቸውን የጣሊያን ፖሊሶች አረጋግጠዋል።
ሜዲትራኒያን ባህር ላይ አደጋ ላይ ያሉ ጀልባዎችን እየተከታተለ የእርዳታ ጥሪ የሚያስተላላፈው “አላርም ፎን” የተባለ ዓለም አቀፍ በጎ ፈቃደኛ ቡድን ሰላሳ አንድ ሰዎች ያሰፈረው አንደኛው ጀልባ ቱኒዥያ ጠረፍ ላይ እንደሰጠመ አመልክቷል። ሰባት ተሳፋሪዎች ተደርሶላቸው ህይወታቸው የተረፈ ሲሆን ሁለት ሰዎች ሰጥመዋል፣ ሃያ ሁለቱ ደግሞ አልተገኙም።
የተመድ የፍልሰተኞች ድርጅት /አይኦኤም/ እንዳመለከተው በእአአ 2021 ብቻ ከሰሜን አፍሪካ ተነስተው አውሮፓ ለመግባት በጀልባ የተሳፈሩ ከ1,300 የሚበልጡ ፍልሰተኞች ህይወታቸውን አጥተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮምሽነር /ዩኤንኤችሲአር/ በበኩሉ ባለፈው የእአአ 2020 ባህሩን አቋርጠው ጣሊያን የደረሱት 34,154 ስደተኞች ሲሆኑ በንፅፅር ዘንድሮ 47,932 መድረሳቸውን አመልክቷል።