ጣሊያን ፍልሰተኞችን አልባኒያ ውስጥ ወደሚገኙ የስደተኞች ማቆያ ማዕከሎች ለመላክ የያዘችው አወዛጋቢ እቅድ በዚህ ሳምንት አንድ የሮም ፍርድ ቤት የድርጊቱን ህጋዊነት አስመልክቶ ማብራሪያ ለመጠየቅ ወደ የአውሮፓ ሕብረት ችሎት መምራቱን ተከትሎ፤ ፈተና ገጥሞታል። የአውሮፓ ሕብረት ዳኞች በጉዳዩ ላይ ብይን እስኪሰጡ ድረስም ወራት ወይም አመታት ሊወስድ መቻሉ ተመልክቷል።
የፍልሰተኞችን ጉዳይ የሚመለከተው የሮሙ ልዩ ችሎት ዳኞች የጣሊያን መንግስት ወደዚያች አገር የሚጎርፈውን ፍልሰተኛ አልባኒያ ውስጥ ወደሚገኙ የስደተኞች ማቆያዎች ለመላክ ፍቃድ እንዲሰጠው ለችሎቱ ባቀረበው ጥያቄ ላይ ብይን ለመስጠት ባለመፍቀዱ ነው ሉክሰምበርግ ወደሚገኘው የአውሮፓ ህብረት ፍርድ ቤት ጉዳዩን የመራው።
የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎም የጣሊያኑን ፍርድ ቤት ዳኞች ውሳኔ በመተቸት በኤክስ ማሕበራዊ መልዕክት መላላኪያ ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት አሜሪካዊው ቢሊየነር ኤላን መስክ ከጣሊያኑ ፕሬዝዳንት ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ገብተዋል።
ጣሊያን ወደ ድንበሯ የሚያቀኑትን እና ከባሕር የምትታደጋቸውን ፍልሰተኞች በቀጥታ ወደ አልባኒያው ማቆያ ማእከላት ለማጓጓዝ የወሰነችው የጥገኝነት ጥያቄዎቻቸውን ለመከታተል እና የጥገኝነት ጥያቄያቸው ውድቅ የተደረገባቸውን በዚያው ፍጥነት ወደ ትውልድ ሀገራቸው ለመመለስ በማቀድ ነው።
በዚህም መሰረት አልባኒያ ውስጥ ሁለት የስደተኞች ማቆያ ማዕከላት የገነባችው ጣሊያን በሚቀጥሉት አምስት አመታት ውስጥ ለምታካሂደው ሥራም ከ650 ሚሊየን ዶላር በላይ ያስወታጣል ተብሎ ተገምቷል። የጣሊያን የድንበር ዞኖች ተብለው የተሰየሙት ሁለቱ ማዕከሎች የሚተዳደሩት በጣሊያን ባለስልጣናት መሆኑም ታውቋል።
መድረክ / ፎረም