የጣልያን ፖሊስ፣ ትላንት ረቡዕ፣ በሕገ ወጥ የሰዎች ማዘዋወር የጠረጠራቸውን 29 ግለሰቦችን መያዙን አስታወቀ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ፣ ለዓመታት፣ ድንበር ተሻጋሪ ፍልሰተኞችን፣ በባሕር ወደ ጣልያን አስርገው ከአስገቡ በኋላ፣ ወደ ሰሜን አውሮፓ ሲያጓጉዟቸው እንደኖሩ፣ ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል፡፡
የሕገ ወጥ ማስተላለፍ ተጠርጣሪዎቹ የተያዙት፣ ብዙዎቹ ፍልሰተኞች፥ ከቱርክ ወይም ከግሪክ ተጓጉዘው ለመጀመሪያ ጊዜ ይደርሱበታል በተባለውና በጣልያኑ ባሕረ ገብ ምድር በምትገኘው ካላብሪያ ደሴት፣ በዐቃብያነ ሕጎች መሪነት፣ ለአራት ዓመታት ያህል በተካሔደ ክትትል መኾኑ ተጠቅሷል፡፡
በቱርክ፣ በግሪክ፣ በቤልጅየም፣ በጀርመን፣ በስዊድን፣ በእንግሊዝ እና በሞሮኮ የሚገኙ ተባባሪ አካላትም፣ በክትትሉ ላይ ተሳታፊ እንደኾኑ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ፍልሰተኞቹ፣ ለሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎቹ፣ እስከ 15ሺሕ ዩሮ ወይም 16ሺሕ 500 ዶላር እንደሚከፍሉም መርማሪዎቹ ገልጸዋል፡፡
በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተጠርጣሪዎች፣ ሕገ ወጥ ስደትን በማበረታታት እና ወደ 30 ከሚጠጉ የባሕር ጉዞዎች ጋራ በተያያዘው ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ሊከሠሡ እንደሚችሉ ፖሊስ አመልክቷል፡፡
አብዛኞቹ የባሕር አስተላላፊዎች(የጀልባ ላይ ሠራተኞች)፣ ከዩክሬን ወይም ከቀድሞ የሶቭየት ኅብረት አገሮች መኾናቸው ሲገለጽ፣ የዝውውር መሥመሩን የሚመሩት ዋናዎቹ ተጠርጣሪዎች ደግሞ፣ ከኢራቅ እና ከኩርድ አካባቢዎች መኾናቸውን፣ የጣልያን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል፡፡
ከሕገ ወጥ ተጓዦቹም፣ ከእስያ ወይም ከመካከለኛ ምሥራቅ የኾኑቱ እንደሚበዙበት ፖሊስ ገልጿል፡፡