በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ደስታንና መከፋትን ያሳደረው የትረምፕ የእሥራኤል ጉብኝት


ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ እሥራኤልን ከጎበኙ በኋላ አይሁዱ ደስተኞች ቢሆኑም ፍልስጥዔማዊያኑ ግን የተከፉ መሆናቸውን እየገለፁ ነው፡፡

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ እሥራኤልን ከጎበኙ በኋላ አይሁዱ ደስተኞች ቢሆኑም ፍልስጥዔማዊያኑ ግን የተከፉ መሆናቸውን እየገለፁ ነው፡፡

ለላንቲካ ወይም ለይስሙላ ወይም ለመታያ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በቁም ነገር በሚታዩባት እሥራኤል የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ያከናወኗቸው እጅግ ከፍተኛ ትርጉም የተሰጣቸው አድራጎቶች እሥራኤላዊያኑን ከልብ አስፈንድቀዋል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁን ጨምሮ፡፡ «ለአይሁድ ሕዝብና ለአይሁድ መንግሥት ላለዎ እጅግ የጠነከረ ወዳጅነት አመሰግንዎታለሁ» ብለዋቸዋል የእሥራኤሉ መሪ፡፡

ትረምፕ በአይሁድ እምነት እጅግ ቅዱስ የሆነውን የፅዮን ቤተ-መቅደስ ምዕራባዊ ግንብ ሲጎበኙ የመጀመሪያው ተቀማጭ ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡

ከእርሣቸው የቀደሙት የአሜሪካ መሪዎች ሁሉ ከዚያ ርቀው መቆየት የመረጡት ፍልስጥዔማዊያኑ የመጭ ሃገራቸው ማዕከል፤ የመንግሥታቸው መናገሻ ናት ብለው ለሚያምኑት አወዛጋቢ ለሆነው የአሮጌዪቱ ኢየሩሳሌም የእሥራኤል ይዞታነት ዕውቅና መስጠት ባለመፈለጋቸው እንደሆነ ይነገራል፡፡

ትረምፕ በሃያ ስምንት ሰዓታት ቆይታቸው እጅግ የበረከተ ሙገሳና ክበትን በእሥራኤል ላይ ሲነሰንሱ በዌስት ባንክ ከተማዪቱ ቤተልሄም ያሳለፉት ግን ከፍልስጥዔም ፕሬዚዳንት ማኅሙድ አባስ ጋር የተሰበሰቡበትን አንድ ሰዓት ብቻ ነው፡፡

«የሰላም ጊዜው ደርሷል» ቢሉም ትረምፕ፤ ሰላሙ እንዴት እንደሚጨበጥ የሚያመላክት ዝርዝር ዕቅድ ግን አላቀረቡም፡፡

ፍልስጥዔማዊያን እጅግ ስለሚያሳስቧቸው ጉዳዮች ወይም ስለሚመኟቸው ሕልሞቻቸው፤ ስለአይሁዳዊያኑ የሠፈራ መስፋፋት ወይም ስለ ፍልስጥዔማዊ መንግሥት ምሥረታ አንድም ቃል አልወጣቸውም፡፡

የትረምፕ ጉብኝት መከፋትን እንዳሳደረበት የተናገረው የዌስት ባንኩ ተማሪ ኢማን ሃዳድ «ለአሜሪካዊ ፕሬዚዳንት የተለመደ ጉብኝት ነው፤ በኔ ሃሣብ፡፡ በንግግራቸው ውስጥ ስለ ሠፈራ፣ ስለእሥራኤል የኃይል ይዞታ፣ ስለኬላዎቹ ምንም አልሰማሁም፡፡ ምንም አዲስ ነገር የለም» ብሏል፡፡

በድርድር፣ በፅናት፣ ከአንተም ይህ ይቅር ከእኔም ይህ ይቅር በመባባል ወገኖቹ ለሰላም ሊሰማሙ እንደሚችሉ ትረምፕ ተናግረዋል፡፡ እንደመጀመሪያ እርምጃ ተጠራጣሪዎቹን የእሥራኤልና የፍልስጥዔም ተደራዳሪዎች ወደ ንግግር ጠረጴዛ ለመመለስ እየጣሩ ነው፡፡ ምናልባት ሊሳካለቸው ይችል ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ለፕሬዚዳንቱ እምቢ ለማለት የከጀለ ያለ አይመስልም፡፡

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡

ደስታንና መከፋትን ያሳደረው የትረምፕ የእሥራኤል ጉብኝት
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:47 0:00

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG