ዩናይትድ ስቴትስ፣ ካታር እና ግብፅ እስራኤል እና ሃማስ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ እየገፋፏቸው ባለበት ወቅት የእስራኤል ወታደሮች ዛሬ አርብ በደቡባዊ ጋዛ ካን ዮኒስ ከተማ አዲስ ጥቃት ሰንዝረዋል።
የእስራኤል ኃይሎች የሚያካሂዱት ተደጋጋሚ ጥቃት ቢሰነዘርባቸውም አሁንም በአካባቢው እንደሚንቀሳቀሱ የሚናገሩትን የሃማስ ተዋጊዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መሆኑን ተናገረዋል።
የእስራኤል ወታደሮች ባለፈው ሀምሌ ጥቃት ከሰነዘሩበትና ከባድ ውድመት ከደረሰበት ምስራቃዊ ካን ዩኒስ ከተማ ሸሽተው ወዲህ ከመጡ ገና ሁለት ሳምንት ያልሞላቸውን ብዙዎቹን ተፈናቃይ ፍልስጤማውያን አሁንም ያሉበትን ከተማ ለቀው እንዲወጡ ታዘዋል፡፡ እስራኤል ያሳለፈችው ይህ ትእዛዝ ሌላ ትልቅ የፍልስጤማውያንን ፍልሰት አስከትሏል።
ትላንት ሀሙስ በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማዊያን መሰረታዊ የሆኑ ትናንሽ የጋዝ ምድጃዎች፥ፍራሾች፥ ድንኳኖች፣ ቦርሳዎች እና ብርድ ልብሶች የመሳሰሉትን መገልገያዎች በመያዝ ሸሽተዋል።
የእስራኤል እና የአሜሪካ ባለስልጣናት አዲስ የተሰየመው የሃማስ መሪ እና እ.ኤ.አ ኦክቶበር 7 በእስራኤል ላይ በተፈጸመው ጥቃት ቁልፍ ሰው የሆነው ያህያ ሲንዋር በካን ዮኒስ ስር ባሉ ዋሻዎች ውስጥ ተደብቆ ሊሆን ይችላል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
የእስራኤል ጦር ዛሬ አርብ ባወጣው መግለጫ ተዋጊ አውሮፕላኖች በካን ዮኒስ ተዋጊዎች እና የጦር መሳሪያዎች ማከማቻ ናቸው ያሏቸውን ጨምሮ 30 የሃማስ ኢላማዎችን መምታታቸውን ገልፆ፥ የምድር ወታደሮቹ ደግሞ ዋሻዎችን እና ሌሎች የሀማስ መሠረተ ልማቶችን አስሰዋል ብሏል።
የቀድሞ የሃማስ መሪ እስማኤል ሃንዬ በእስራኤል እንደሆነ በተገመተ የቦምብ ጥቃት እኤአ ሀምሌ 31 ከተገደሉ በኋላ አስር ወራት የጋዛ ጦርነት በኋላ የተኩስ አቁም እንዲደረግ በሶስተኛ ወገን የሚካሄደው የሸምጋዮቹ ግፊት እንዲቀጥል የታቀደ ይመስላል፡፡
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታኒያሁ ጽ/ቤት ትላንት ሀሙስ ተደራዳሪዎችን እኤአ ነሀሴ 15 ወደ ካታር ዋና ከተማ ዶሃ ወይም ወደ ግብጽ መዲና ካይሮ እንደሚልክ አስታውቋል፡፡
በእስካሁኑ ድርድር ቁልፍ ሚና በነበራቸው በቀደሞው መሪው ሟቹ እስማኤል ሀንዬን ምትክ ሲንዋር እንደተተኩ ባላፈው ማክሰኞ ያስታወቀው ሀማስ ማንን እንደሚልክ አላሳወቀም፡፡
ይሁን እንጂ ቡድኑ ውስጥ እንደ ብርቱ ሰው የሚታዩትና በሃማስ ስትራቴጂም ውስጥ ቁልፍ ተሳትፎ እንዳላቸው የሚገመቱት የሲንዋር ወደ ከፍተኛ አመራር ማደግ በድርድሩ ላይ ተጽእኖ ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋት አድሯል፡፡
መድረክ / ፎረም