እስራኤል በጋዛ ባካሄደችው ወታደራዊ ጥቃት ቢያንስ 30 ሰዎች መገደላቸውንና አብዛኞቹ በከበባ ስር በሚገኘው ኑሴይራት መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የነበሩ መሆናቸውን የህክምና ባለሙያዎች አስታወቁ፡፡
የህክምና ባለሞያዎች ይህን ያሉት አካባቢውን ወረው የነበሩት የእስራኤል ታንኮች አርብ እለት ካፈገፈጉ በኃላ ነው።
የጤና ባለሞያዎቹ አክለው፣ ከሩሴይራት በስተሰሜን በሚገኙ አካባቢዎችም የ19 ፍልስጤማውያን አስክሬኖችን ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
የእስራኤል ታንኮች አሁንም ከመጠለያ ጣቢያው በስተምዕራብ መኖራቸውን የገለጸው የፍልስጤም የሲቪል የአደጋ ጊዜ አገልግሎት፣ ቡድኑ ከዛ አካባቢ ለሚደርሰው የእርዳታ ጥሪዎች ምላሽ ለመስጠት አለመቻላቸውንም ጨምሮ ገልጿል፡፡
ጥቃቱን አስመልክቶ በእስራኤል ጦር በኩል እስካሁን የተሰጠ አዲስ ምላሽ ባይኖርም፣ ሠራዊቱ "በጋዛ ሠርጥ ውስጥ የሚያካሄደው ዘመቻ አካል የሆኑ የሽብር ዒላማዎችን መምታቱን" ቀጥሏል ሲል ትላንት ሃሙስ አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል ባለስልጣናት ባለፉት ወራት በጋዛ ባካሄዱት ጥቃት ይዘዋቸው የነበሩ ሰላሳ ፍልስጤማውያንን መልቀቃቸውን አስታውቀዋል፡፡ የህክምና ባለሙያዎችም የተለቀቁት ሰዎች በደቡባዊ ጋዛ ከሚገኝ ሆስፒታል ለህክምና ምርመራ መድረሳቸውን አረጋግጠዋል፡፡
በጦርነቱ ወቅት የታሰሩ ፍልስጤማውያን ከእስር ከተፈቱ በኋላ በእስር ወቅት በእስራኤላውያን እንግልት እና የማሰቃየት ተግባር እንደሚፈጸምባቸው ተናግረዋል። እስራኤል ግን ይህንን የማሰቃየት ውንጀላ አትቀበልም፡፡
ለወራቶች በጋዛ የተኩስ ማቆም ስምምነት እንዲደርሰ ሲደረጉ የነበሩ ውይይቶች እምብዛም ለውጥ ያላሳዩ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ድርድሮቹ ቆመዋል።
በእስራኤል እና የሐማስ አጋር በሆነው የሊባኖሱ ሂዝቦላህ መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ከረቡዕ ማለዳ ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን፣ ከቅርብ ወራት ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ ተባብሶ የነበረውንና የጋዛን ግጭት ሸፍኖት የነበረውን ጦርነት ማስቆም መቻሉ ተገልጿል፡፡
መድረክ / ፎረም