በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ የተጀመረው የአደራዳሪዎች ጥረት ብዙም ለውጥ ያላሳየ ሲሆን የእስራኤል ወታደሮች በራፋህ በአየር እና በመሬት የሚያደርጉትን ከባድ ጥቃት ቀጥለው ወደ ምዕራብ ለመግፋት እየሞከሩ መሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
ነዋሪዎች እንደገግለጹት ትናንት ሌሊቱን በእስራኤል ወታደሮች እና በሐማስ በሚመራው የፍልስጤም ተዋጊዎች መካከል ከፍተኛ የተኩስ ልውውጦች ተካሂደዋል። ከግብፅ ጋር የሚያዋስነውን ድንበር የተቆጣጠሩት የእስራኤል ታንኮች ወደ ምዕራብ ደቡባዊቷ ከተማ መሃል ድንገተኛ ጥቃቶችን በማድረስ በቤታቸው የሚገኙ በርካታ ነዋሪዎችን አቁስለዋል ሲሉም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
ሌሊቱን ቤታቸው ውስጥ ጥቃት ከደረሰባቸው በተጨማሪ ብዙ ነዋሪዎችም በጧት እየተነሱ መኖሪያቸውን ትተው መፈናቀላቸው ተገልጿል፡፡ የእስራኤል ወታደሮች ሌሎች ሁለት ካምፖችን ጨምሮ በማዕከላዊ ጋዛ የሚገኘው አል ቡሬጅ ካምፕ ውስጥ ዘልቀው መግባታቸውን እና በአቅራቢያው ያለ ከተማን በቦምብ በመደብደብ ብዙ ጉዳት ማድረሳቸውን የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል።
ሐማስ፣ ኢስላሚክ ጂሃድ እና ሌሎች ቡድኖች በማዕከላዊ እና በደቡብ ጋዛ በእስራኤል ወታደሮች ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውንም በዘገባው ተጠቅሷል። በዩናይትድ ስቴትስ የሚደገፉ የካታር እና የግብፅ ሸምጋዮች ጦርነቱን ለማስቆም እንዲሁም የእስራኤል ታጋቾችን እና በእስራኤል የታሰሩ ፍልስጤማውያንን ለማስፈታት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲኖር ለማደራደር እየሞከሩ ቢሆንም እስካሁን ምንም ለውጥ አልታየም፡፡
በህዳር ወር ከተደረገው የአጭር ጊዜ የተኩስ አቁም ስምምነት በኋላ ሌላ የተኩስ አቁም ለማድረግ የተደረገው ሙከራ አልተሳካም፣ ሐማስ ግጭቱን በዘላቂነት እንዲቆም ሲጠይቅ እስራኤል ስምምነቱ ጊዚያዊ ብቻ እንዲሆን ትፈልጋለች፡፡
መድረክ / ፎረም