በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የእስራኤል ዲፕሎማት ከአፍሪካ ኅብረት ዓመታዊ ጉባዔ መገለላቸውን የኅብረቱ ሊቀመንበር አረጋገጡ


የእስራኤል ዲፕሎማት ከአፍሪካ ኅብረት ዓመታዊ ጉባዔ መገለላቸውን የኅብረቱ ሊቀመንበር አረጋገጡ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:37 0:00

የእስራኤል ዲፕሎማት ከአፍሪካ ኅብረት ዓመታዊ ጉባዔ መገለላቸውን የኅብረቱ ሊቀመንበር አረጋገጡ

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔን ለመታደም በሚያስችል ልዩ ፈቃድ አሰጣጥ ዙሪያ በተነሳ ውዝግብ ምክንያት አንድ ከፍተኛ የእስራኤል ዲፕሎማት ቅዳሜ ዕለት ከተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ እንዲወጡ ተደርገዋል።

በተለያዩ የኢንተርኔት ድህረገፆች የሚዘዋወሩ ምስሎችም የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ መክፈቻ እየተካሄደ የፀጥታ አባላት ዲፕሎማቷን ከአዳራሹ ከማስወጣታቸው በፊት በጥያቄ ሲያጣድፏቸው ያሳያሉ።

በጉዳዩ ላይ ለሚዲያ አስተያየታቸውን የሰጡት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማኻማት፣ በእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ክፍል ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት አምባሳደር ሻሮን ባር ሊ ስብሰባውን ለመታደም የሚያስችለውን ፈቃድ እንዴት በስህተት እንዳገኙ የሚያጣራ ምርመራ እንደሚጀመር ገልፀዋል።

"አንድም እስራኤላዊ ወደዚህ ጉባኤ አልጋበዝንም። አንድ ሰው ግን የመግቢያ ልዩ ፈቃዱን ይዞ ወደ አዳራሹ መግባቱን አውቀናል፣ አዳራሹን በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡም ጠይቀናል። እኝህ ግለሰብ በኢትዮጵያ የሚኖሩ አይደሉም።

ስለዚህ እንዴት ልዩ ፈቃዱን ሊያገኙ እንደቻሉ ለማጣራት ምርመራ እያደረግን ነው።” ካሉ በኋላ “ስለዚህ የሚዲያ አባላት የሆናችሁ እንድታውቁ የምንፈልገው የትኛውንም የእስራኤል ባለስልጣን እንዳልጋበዝን ነው። ስህተቱ ከየት እንደመጣ ለማወቅ ይህን ምርመራ እስከመጨረሻው እንገፋዋለን።" ብለዋል።

እስራኤል ግን ለድርጊቱ 55 ሀገሮችን የያዘው አህጉራዊ ስብስብ አባል የሆኑትን ደቡብ አፍሪካን እና አልጄሪያን በ"ጥላቻ" ተገፋፍተው የአፍሪካ ኅብረትን መያዣ አድርገውታል ስትል ተጠያቂ አድርጋለች።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባወጣው መግለጫም "የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ሻሮን ባር ሊ የታዛቢነት ልዩ የመግቢያ ፈቃድ ይዘው ሳለ ከአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ አዳራሽ እንዲወጡ የተደረገበትን ሁኔታ እስራኤል በጥሩ ሁኔታ አትመለከተውም" ብሏል።

መግለጫው አክሎ እስራኤል የሚገኘው የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ጉዳይ አስፈፃሚ ተጠርጠው ግሳጼ እንደሚሰጣቸው አመልክቶ "የእስራኤልን የታዛቢነት ሚና ለመሰረዝ የተደረገው ሙከራ በድርጅቱ ህግ መሰረት የለውም" ብሏል።

ደቡብ አፍሪካ በበኩሏ የእስራኤልን ውንጀላ ውድቅ አድርጋ፣ እስራኤል ለአፍሪካ ህብረት ታዛቢነት ያቀረበችው ማመልከቻ በህብረቱ ውሳኔ አለማግኘቱን ገልፃለች። በደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ግንኙነት

ክፍል የህዝብ ዲፕሎማሲ ኃላፊ የሆኑት ክሌይሰን ሞኒየላ ለሮይተርስ ሲናገሩ "የአፍሪካ ህብረት ለእስራኤል የታዛቢነት ማዕረግ ለመስጠት ውሳኔ እስካልሰጠ ድረስ ሀገሪቱ መቀመጫ ይዛ ታዛቢ መሆን አትችልም" ያሉ ሲሆን "ጉዳዩ የደቡብ አፍሪካ ወይም የአልጄሪያ ሳይሆን የመርህ ጉዳይ ነው" ሲሉ አብራርተዋል።

ታሪክ እንደሚያሳየው የደቡብ አፍሪካ ገዢ ፓርቲ የፍልስጤም ትግል ጠንካራ ደጋፊ ነው። በአፍሪካ ህብረት የተወከለውን የአልጄሪያ ልዑካን ቡድን በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመጠየቅ ወዲያውኑ ማግኘት አልተቻለም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአፍሪካ ህብረት 36ኛ መደበኛ የመሪዎች ጉባዔ እሁድ እለት ከመጠናቀቁ በፊት መሪዎች በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ስላለው አሳሳቢ የፀጥታ ሁኔታ መነጋገራቸውን የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ገልፀዋል።

"በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሰላም እና ፀጥታ ጉዳይ በመሪዎች ድረጃ ስብሰባ አድርገናል። የምስራቅ አፍሪካን ኮማንድ ፖስት ባለቤት እንዲሆን እና በቀጠናው ያለውን የፀጥታ ሁኔታ በኃላፊነት እንዲቆጣጠር አቅሙን ማጠናቀር እንፈልጋለን።"

በጉባዔው ማጠናቀቂያ ፋኪ በሰጡት መግለጫ፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ የሰላም እና ፀጥታ ጉዳይ የተሰበሰቡት መሪዎች በምስራቅ ኮንጎ የሰፈረውን የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ኃይል አቅም ለማጠናከር መወሰኑን አስታውቀዋል።

XS
SM
MD
LG