በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ ባወጣ ማግሥት እስራኤል ጋዛን አጠቃች


ከጋዛ ከተማ በስተደቡብ የእስራኤል ጥቃትን ተከትሎ ፍልስጤማውያን የህንፃውን ፍርስራሽ እየፈተሹ፤ እአአ ኅዳር 22/2024
ከጋዛ ከተማ በስተደቡብ የእስራኤል ጥቃትን ተከትሎ ፍልስጤማውያን የህንፃውን ፍርስራሽ እየፈተሹ፤ እአአ ኅዳር 22/2024

የዓለም አቀፍ ወንጀል ፍርድ ቤት የጋዛን ጦርነት አስመልክቶ የእሥር ማዘዣ ባወጣ ማግሥት ዛሬ ዓርብ በሰሜን ጋዛ የሚያካሂደውን የተጠናከረ ጥቃት የቀጠለው የእስራኤል ጦር እአአ ጥቅምት 7 ቀን 2023 እስራኤል ውስጥ በተፈጸመው አሰቃቂ ጥቃት የተሳተፉ ሁለት የሃማስ አዛዦችን ጨምሮ አምስት የሃማስ ታጣቂዎች መግደሉን አስታውቋል፡፡

በሰሜን ጋዛ የሚካሄደው ጥቃት አካል ሆኖ፣ በደቡብ ቤይሩት የሂዝቦላ ምሽግ ላይ ያነጣጠረ የአየር ጥቃት መፈጸሙንም የእስራኤል ጦር አስታውቋል፡፡

ሊባኖስ ውስጥ በኢራን ከሚደገፈው የሃማስ አጋር ከሂዝቦላህን ጋራ የምትዋጋው እስራኤል ዛሬ ዓርብ በቤይሩት ደቡባዊ ዳርቻ በርካታ ጥቃቶች ማድረሷን የፈረንሳይ የዜና ወኪል ቴሌቭዥን በቀጥታ ያስተላለፈው ዘገባ አሳይቷል፡፡

የህክምና ባለሞያዎች “እስራኤል ሌሊቱን በሰሜን ጋዛ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ዒላማ ከሆኑት መካከል ፣ በቤተ ላህያ እና በአቅራቢያው ጃባሊያ በርካታ ሰዎች ተገድለዋል ወይም የደረሱበት ጠፍቷል” ብለዋል።

የሰላማዊ ሰዎች ተከላካይ ድርጅት በጥቃቱ ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ አልገለጸም፡፡

ትላንት ሐሙስ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ እና የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትራቸው ዮአቭ ጋላንት ረሀብን ለጦርነት መጠቀሚያ የማዋል ወንጀል እና በተከበበችው ጋዛ በሚገኙ ፍልስጤማዊያን ላይ በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል "ኃላፊነት” ሳይኖርባቸው አይቀርም ብሏል፡፡

የሄጉ የዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ ከተለያዩ የዓለም ሀገሮች የተለያዩ አስተያየቶችን አስከትሏል፡፡ አንዳንድ መሪዎች የእስር ማዘዣ የወጣባቸው እስራኤላውያን "ወደ ሀገራችን ግዛት ከገቡ በቁጥጥር ስር እናውላቸዋለን" ብለዋል ፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ጨምሮ ሌሎች መሪዎች በበኩላቸው የእስራኤል መሪ “በጸረ ሴማዊ የእስራኤል ጥላቻ የተመራ” እና “ትርጉም የሌለው” ሲሉ የጠሩትን ውሳኔ ተቃውመዋል፡፡

እስራኤል ከሃማስ ጋራ በምታካሂደው ጦርነት ባለፈው ታኅሣስ በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የተመሰረተባትን የዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ እና ባለፈው ሳምንት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ ኮሚቴ የቀረባባትን ዘገባ ተቃውማለች፡፡

ሃማስ እና ሂዝቦላ በዩናይትድ ስቴትስ፣ ብሪታንያ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና ሌሎች በአሸባሪነት የተፈረጁ ናቸው።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG