በእስራኤል፥ መንግሥት “የፍትሕ ሥርዐቱን ለማሻሻል” በሚል ያወጣው ዕቅድ፣ በፓርላማ መጽደቁን ተከትሎ፣ የአገሪቱ ዜጎች፣ በቀኝ ወግ አጥባቂው መንግሥት ላይ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ናቸው።
በንግድ መዲናዋ ቴል አቪቭ፣ ፖሊስ፥ በደርዘን የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎችን እንደያዘ አስታውቋል። በዋና አውራ ጎዳናዎች እና በቴል አቪቭ አየር ማረፊያ፣ ትላንት ማክሰኞ ተቃውሞ ሲደረግ ውሏል።
ዐዲስ በተሻሻለው ሕግ፣ የፍትሕ አካሉ፥ መንግሥት የሚያሳልፋቸውን ውሳኔዎች የመሻር ሥልጣኑ እንዲገታ ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም፣ በዳኞች ሹመት መንግሥት የበለጠ ሚና እንዲኖረው ያደርጋል፤ ተብሏል።
ተቃዋሚዎች ርምጃው፥ “ዴሞክራሲን ያዳክማል፤” ሲሉ ተችተዋል። በሙስና ተጠርጥረው በፍርድ ሒደት ላይ የሚገኙት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሁ፣ በእርሳቸው ላይ ሊመጣ ያንዣበበውን ፍርድ ለማምለጥ የቀየሱት ዘዴ ነው፤ ሲሉ ተቃዋሚዎቹ አክለው ይከሣሉ። ናታንያሁ ክሡን ያስተባብላሉ።
መድረክ / ፎረም