ከሁለት ሳምንት የምድርና የአየር ጥቃት በኋላ፣ የእስራኤል ጦር የሺፋ ሆስፒታል እና አካባቢውን ለቆ ወጥቷል። ሁለት መቶ የሚሆኑ ታጣቂዎችን መግደሉን እና ሌሎች በመቶ የሚቆጠሩትን ደግሞ መያዙን የአገሪቱ ጦር አስታውቋል።
ስድስት ወር ሊሆነው በተቃረበው ጦርነት፣ በሺፋ ሆስፒታል ላይ የተደረገው ዘመቻ ከፍተኛ ውጤት የተገኘበት እንደሆነ የእስራኤል ጦር አመልክቷል።
በዘመቻው ከፍተኛ የሃማስ መሪዎች እንደተገደሉ፣ መሣሪያ እንደማረከ እና ጠቃሚ የደህንነት መረጃዎችን እንዳገኘም የእስራኤል ጦር ቢያስታውቅም፣ የፍልስጤም ነዋሪዎች በርካታ ሰዎች መገደላቸውን እና ከፍተኛ ውድመት መድረሱን ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግስታት የጤና ድርጅት በበኩሉ 20 የሚሆኑ ታካሚዎች በዘመቻው መገደላቸውንና በደርዘን የሚቆጠሩ ደግሞ ለአደጋ እንደተጋለጡ አስታውቋል። ሐማስ ሆስፒታሉን ለወታደራዊ ዓላማ ይጠቀማል ስትል እስራኤል ትከሳለች፡፡ የጋዛ የሆስፒታል ባለሥልታናት ክሱን ያስተባብላሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአስር ሺሕዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ትናንት እሁድ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁን በመቃወም ሰልፍ አድርገዋል። የታገቱትን እስራኤላውያን ለማስለቀቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጨማሪ ጥረት እንዲያደርጉም ሰልፈኞቹ ጠይቀዋል። ጦርነቱ ከጀመረ ወዲህ የተደረገ ትልቁ የተቃውሞ ሰልፍ ነው ተብሏል።
እስከ አሁን በተደረጉት ውጊያዎች፣ እስራኤል ከባድ ጥቃት የሰነዘረችባቸውን ቦታዎች ጨምሮ፣ ሐማስ አሁንም የመቋቋም ብቃት እንዳለው አሳይቷል ሲል አሶስዬትድ ፕሬስ በዘገባው አመልክቷል።
መድረክ / ፎረም