የእስራኤል የፀጥታ ኃይሎች ሁለት ፍልስጤማዊ ተዋጊዎችን ዛሬ ዌስት ባንክ ውስጥ መግደላቸውን የፍልስጤሙ ወገን ሲያስታውቅ፣ የእስራኤል ሰራዊት ደግሞ ግድያው በመኪና ሆነው ወደ ወታደሮቹ በመተኮሳቸው በተሰጠ የአጸፋ ተኩስ ምክንያት የመጣ ነው ብሏል።
“ናብሉስ” በተባለችው ከተማ ውስጥ ባለ የወታደሮች ኬላ ላይ አንድ አልፎ ሂያጅ መኪና ተኩስ ከከፈተ በኋላ “ሁለት ተጠርጣሪ መኪኖች” ላይ ተኩስ መክፈታቸውን የእስራኤል ሰራዊት አስታውቋል። በተኩሱ የተጎዳበት ወታደር እንደሌለ ሰራዊቱ ጨምሮ ገልጿል።
በእስራኤል በተያዘችው ዌስት ባንክ ውስጥ ላለፉት ጥቂት ወራት ግጭትና ግድያ እየተባባሰ ይገኛል።
የፍልስጤም የጤና ሚኒስቴር ሟቾቹ የ35 እና የ47 ዓመት እድሜ ያላቸው ወንዶች መሆናቸውንና ሦስተኛ ሰው መቁሰሉም አስታውቋል።
የፍልስጤሙ ፕሬዚዳንት ማህሙድ አባስ ንቅናቄ የፋታህ ቅርንጫፍ የሆነው አል-አቅሳ ብርጌድ፣ የተገደሉት ሁለቱ ወታደሮች አባላቱ መሆናቸውን አስታውቋል።