በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የራፋ የደንበር መውጫ ከጦርነቱ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከፈተ


የእስራኤል የአየር ጥቃት ተከትሎ ፍልስጤማውያን በፈራረሱ ህንፃዎች ስር በህይወት የተረፉ ካሉ እየፈለጉ፤ ሰሜን ጋዛ ሰርጥ በጃባሊያ የስደተኞች ካምፕ እአአ ኅዳር 1/2023
የእስራኤል የአየር ጥቃት ተከትሎ ፍልስጤማውያን በፈራረሱ ህንፃዎች ስር በህይወት የተረፉ ካሉ እየፈለጉ፤ ሰሜን ጋዛ ሰርጥ በጃባሊያ የስደተኞች ካምፕ እአአ ኅዳር 1/2023

የእስራኤል-ሐማስ ጦርነት ከተባባሰ ወዲህ፣ የጋዛ-ግብጽ ደንበር፣ በራፋ ለሚገኙ የውጭ ሀገራት ዜጎች፣ ዛሬ ረቡዕ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከፍቷል፡፡ የራፋ መሻገሪያ መከፈት፣ እስራኤል፣ ግብጽ እና ሐማስ በኳታር ያደረጉት ስምምነት አካል እንደኾነ ተነግሯል፡፡ ይህን ተከትሎ፣ የውጭ አገር ፓስፖርት ካላቸው መካከል፣ የመጀመሪያዎቹ ቡድን አባላት፣ ከተከበበው የጋዛ መሬት ዛሬ መልቀቅ ጀምረዋል፡፡

በስምምነቱ መሠረት፣ ቢያንስ 400 የውጭ ሀገራት ዜጎች ወደ ግብጽ እንዲሻገሩ እንደሚፈቀድላቸው ተነግሯል፡፡

በተጨማሪም፣ 81 የሚደርሱ የተጎዱ ፍልስጥኤማውያንም፣ በግብጽ ሆስፒታሎች ለመታከም፣ ከጋዛ በአምቡላንስ ተወስደዋል።

ተጎጂዎቹ፣ ጦርነቱ ከተጀመረ እ.ኤ.አ. ጥቅምት 7 ቀን አንስቶ፣ ከጋዛ እንዲወጡ የተፈቀደላቸው የመጀመሪያዎቹ ፍልስጥኤማውያን ናቸው።

በሌላ በኩል፣ በመላው የጋዛ ሰርጥ፣ ኢንተርኔት እና የስልክ ግንኙነቶች ዛሬ ረቡዕ እንደተቋረጡ፣ የፍልስጥኤም ቴሌኮምዩኒኬሽን ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡

ይህ የተገለጸው፣ እስራኤል በሰሜን ጋዛ ጃባሊያ ከተማ፣ በፍልስጥኤም ፍልሰተኞች ካምፕ ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት፣ በትንሹ 50 ሰዎች እንደተገደሉና 150 ሰዎች ደግሞ እንደቆሰሉ፣ የፍልስጥኤም የጤና ባለሥልጣናት ካስታወቁ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ነው።

የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ፣ የአየር ጥቃቱ መፈጸሙን ለሲኤንኤን አረጋግጦ፣ “ከፍተኛ የሐማስ አዛዥ” በአካባቢው እንደነበረ ተናግሯል።

የእስራኤል መከላከያ ኀይል፣ ከቆይታ በኋላ ባወጣው መግለጫ፣ ግለሰቡ ኢብራሂም ቢያሪ እንደኾነ ገልጾ፣ እ.ኤ.አ. ጥቅምት 7 ቀን፣ በደቡብ እስራኤል በሐማስ ታጣቂዎች ለደረሰው የግድያ ግብረ ሽብር ዋና መሪ እንደነበር አውስቷል።

ሐማስ በበኩሉ በሰጠው መግለጫ፣ በካምፑ ውስጥ ምንም ዐይነት አዛዥ እንዳልነበረ ገልጾ፣ በጥቃቱ፣ 400 የሚደርሱ ሰዎች ሙት እና ቁስለኛ እንደኾኑ አስታውቋል፡፡

አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ፣ ዛሬ ረቡዕ እንደዘገበው፣ በአየር ጥቃቱ ከተገደሉት መካከል፣ የውጭ ፓስፖርት የያዙ ሦስት ሰዎችን ጨምሮ ሰባት ታጋቾች እንደሚገኙበት ሐማስ ተናግሯል።

ካለፈው ሳምንት ዐርብ ጀምሮ፣ ለሁለት ቀናት ሙሉ በሙሉ የግንኙነት መቋረጥ ባጋጠማት ጋዛ የተከበበው 2ነጥብ3 ሚሊዮን ሕዝብ ከዓለም በመቆራረጡ፣ ወሳኝ ዓለም አቀፍ የርዳታ አቅርቦቶች እንዳይደርሱት መሰናክል እንደፈጠረ ተመልክቷል፡፡

ግጭቱ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ያስከተለ ሲኾን፣ ከ8ሺሕ500 በላይ ጋዛውያን መሞታቸው ተዘግቧል፡፡ ከእነዚኽም ውስጥ ቀላል የማይባሉት ሴቶች እና ሕፃናት ናቸው።

የራፋ ደንበር እንደገና መከፈቱና የተወሰነ ርዳታ ለጋዛውያን መድረሱ እፎይታን ቢሰጥም፣ የተባበሩት መንግሥታት ግን፣ በቂ አይደለም፤ ይላል።

የእስራኤልን ወታደራዊ ርምጃዎችን የሚያወግዙ መልእክቶች እያደጉ እንደኾኑ ሲነገር፣ ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችም ቀጥለዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፣ በቀጠለው ቀውስ እና የሰብአዊ ርዳታ አቅርቦት ላይ ለመወያየት፣ ከነገ በስቲያ ዐርብ፣ እስራኤልን እንደገና ይጎበኛሉ፤ ተብሏል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG