በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

እስራኤል በጋዛ ለሁለተኛ ቀን የምድር ጥቃት አደረሰች


በደቡብ እስራኤል ድንበር ጋዛ የባህር ዳርቻ አካባቢ በርቀት ጭስ ወደ ላይ ሲወጣ ይታያል እአአ ጥቅምት 27/2023
በደቡብ እስራኤል ድንበር ጋዛ የባህር ዳርቻ አካባቢ በርቀት ጭስ ወደ ላይ ሲወጣ ይታያል እአአ ጥቅምት 27/2023

የእስራኤል ሠራዊት ለሁለተኛ ተከታታይ ቀን የምድር ጥቃት ማድረሱን እና አዲስ የአየር ድብደባም በሐማስ ታጣቂዎች ላይ መፈጸሙ ታውቋል።

በሐማስ ቁጥጥር ሥር ባለው ጋዛ መሠረቱን ያደረገው የጤና ሚኒስቴር፣ በእስራኤል ጥቃት የተገደሉ ናቸው ያለውን 7 ሺሕ የሚደርሱ ሰዎች ስም ዝርዝር አውጥቷል።

የዛሬው የምድር ውጊያ ለአጭር ግዜ የተከናወነ መሆኑን እና ታንኮቿ እና የእግረኛ ወታደሮቿ ከሐማስ ተዋጊዎች ጋር ገጥመው እንደነበር፣ እንዲሁም የጸረ ታንክ መሣሪያዎችን መምታቷን እና ጦሯ ወዲያውኑ ወደ ድንበሯ መመለሷን እስራኤል አስታውቃለች፡፡ ሙሉ የሆነ የምድር ወረራ ለማድረግ ዕቅድ እንዳላት እስራኤል በማስታወቅ ላይ ነች፡፡

ጥቃቱ የተደረገው የጋዛ ነዋሪዎች የምግብ፣ ውሃ እና ሌሎችም አቅርቦቶች እያለቁባቸው ባለበት ወቅት ነው ተብሏል።

በጋዛ 1 ሺሕ የሚገመቱ አስከሬኖች በፍርስራሽ ሥር ተቀብረው እንንደሚገኙና፣ ማንነታቸው ያልተለየው የእነዚህ ሰዎች ቁጥር፣ አጠቃላይ የሟቾች ቁጥር ላይ እንዳልተካተተ የዓለም ጤና ድርጅት ባለሥልጣን የሆኑት ሪቻርድ ፒፐርኮርን አስታውቀዋል። ፒፐርኮርን ምንጫቸው ምን እንደሆነ እንዳልጠቀሱ የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል።

የተመድ የፍልስጤማውያን ፍልሰተኞች የርዳታ እና የሥራ ወኪል በበኩሉ፣ 57 ሠራተኞቹ እንደተገደሉበት እና ከእነዚህም ውስጥ 15ቱ በአንድ ቀን ውስጥ መገደላቸውን አስታውቋል።

የሩሲያን ጨምሮ የታገቱ የውጪ ዜጎችን መለቀቅ አስመልክቶ ለመነጋጋር ፣ የሐማስ ባልሥልጣናት ትናንት ማምሻውን ሞስኮ መግባታቸውን የሩሲያ ዜና አገልግሎቶች የሀገሪቱን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ጠቅሰው ዘግበዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG