በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በጋዛው ሆስፒታል ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ተገደሉ


በተከሰተው ፍንዳታ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ከተገደሉ በኋላ የተጎዳ ሰው ወደ ሆስፒታል እየተወሰደ በጋዛ አል አህሊ አራብ ከተማ
በተከሰተው ፍንዳታ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ከተገደሉ በኋላ የተጎዳ ሰው ወደ ሆስፒታል እየተወሰደ በጋዛ አል አህሊ አራብ ከተማ

በጋዛ አል አህሊ አራብ ከተማ በሚገኝ ሆስፒታል በተፈጸመ የሮኬት ጥቃት፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደተገደሉ ተነገረ፡፡

እስራኤል በጥቃቱ፣ የፍልስጥኤም ታጣቂዎችን ጥፋተኛ ስታደርግ፣ የፍልስጥኤም እስላማዊ ጅሃድ ቃል አቃባይ በበኩሉ፣ “ቡድኑ ተጠያቂ አይደለም፤” ሲል አስተባብሏል፡፡

የሐማስ ታጣቂ ቡድን፣ ትላንት ማክሰኞ ምሽት ባወጣው መግለጫ፣ ፍንዳታው በእስራኤል አየር ኃይል እንደተፈጸመ ገልጿል፡፡ የእስራኤል ጦር በበኩሉ፣ “በተሳሳተ መንገድ በፍልስጥኤማውያን ታጣቂዎች የተተኮሰ ሮኬት ሆስፒታሉ ላይ በማረፉ ነው፤” ብሏል፡፡

የጋዛ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ በፍንዳታው ቢያንስ 500 ሰዎች እንደተገደሉ አስታውቋል፡፡ በሆስፒታሉ ላይ የተፈጸመው ጥቃት፣ በመካከለኛ ምሥራቅ ሀገራት ከፍተኛ ተቃውሞ እንደቀሰቀሰ ተነግሯል፡፡

በዌስት ባንክ የፍልስጥኤም አስተዳደር ፕሬዚዳንት ማሐሙድ አባስን በመቃወም የወጡ ፍልስጥኤማውያንን ለመበተን፣ የጸጥታ አስከባሪዎች አስለቃሽ ጢስ ተጠቅመዋል፡፡

በዮርዳኖስም እንዲሁ የጸጥታ ኀይሎች፣ በእስራኤል ኤምባሲ አካባቢ የተሰበሰበውን ሕዝብ ለመበተን አስለቃሽ ጢስ እንደተጠቀሙ ተገልጿል፡፡

በኢራን የሚደገፈው የሒዝቦላህ ታጣቂ ቡድን፣ ጥቃቱን አውግዞ፣ ዛሬ ረቡዕ፣ በሊባኖስ ትልቅ የተቃውሞ ሰልፍ ጠርቷል። በዚኽ ኹሉ መካከል፣ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ የረጅም ጊዜ የአሜሪካ አጋር ለኾነችው እስራኤል ድጋፋቸውን ለመግለጽ፣ ዛሬ ረቡዕ ቴልአቪቭ ገብተዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ

ባይደን፣ ለእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ፥ “በሆስፒታሉ በደረሰው ፍንዳታ በጣም እንዳዘኑና እንደተበሳጩ” ገልጸው፣ “ካየኹት ነገር ተነሥቼ ድርጊቱ የተፈጸመው በእርስዎ ወገን ሳይኾን፣ በሌላ ቡድን የተደረገ ይመስላል፤” ሲሉ ጥርጣሬያቸውን አመልክተዋል፡፡ ባይደን አክለውም፣ “ይኹን እንጂ፣ ፍንዳታውን ምን እንዳደረሰው ብዙዎች ርግጠኞች አይደሉም፤” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ባይደን፣ ፍንዳታው በእስራኤል ያልደረሰ ስለመኾኑ ያመኑበትን ምክንያት በዝርዝር አልገለጹም፡፡

እስራኤል፣ ራሷን ለመከላከል የሚያስፈልጋት ሁሉ ነገር እንዳላት ለማረጋገጥ ቃል የገቡት የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት፣ ከእስራኤል ቆይታቸው በኋላ ከአረብ መሪዎች ጋራ በዮርዳኖስ አማን ሊያደርጉት የነበረው ስብሰባ፣ የጋዛው ጥቃት ከተሰማ በኋላ ተሰርዟል፡፡

በእስራኤል እና በሐማስ ታጣቂ መካከል እየተካሔደ ባለው ግጭት፣ እስከ አሁን ከ1ሺሕ400 በላይ እስራኤላውያንና ከሦስት ሺሕ በላይ ፍልስጥኤማውያን ተገድለዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG