በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

እስራኤል ከሚሊዮን በላይ የጋዛ ነዋሪዎች በ24 ሰዓት እንዲወጡ ማዘዟን ለተመድ አስታወቀች


የእስራኤል ታንኮች የጋዛ ሰርጥ ድንበር እያቀኑ፤ እአአ ጥቅምት 13/2023
የእስራኤል ታንኮች የጋዛ ሰርጥ ድንበር እያቀኑ፤ እአአ ጥቅምት 13/2023

ሙሉ ጋዛን በመክበብ የእግረኛ ውጊያ ለማድረግ እንደተዘጋጁ የገለጹት የእስራኤል ወታደራዊ ባለሥልጣናት፣ አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሺሕ የሰሜን ጋዛ ሲቪል ነዋሪዎች፣ “ለራሳቸው ደኅንነት” ሲሉ፣ በ24 ሰዓት ውስጥ ወደ ደቡብ ጋዛ እንዲሔዱ ማስጠንቀቂያ እንደሰጡ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

የድርጅቱ ባለሥልጣናት፣ ትላትን ኀሙስ ማምሻውን እንደገለጹት፣ እስራኤል ማስጠንቀቂያውን የሰጠችው፣ በጋዛ ከተማ ለሚገኙ ነዋሪዎችም ጭምር ነው፡፡

የጋዛን ነዋሪዎች በሰብአዊ ጋሻነት እንደሚጠቀም በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ክስ የሚቀርብበት ታጣቂው ሐማስ በበኩሉ፣ የእስራኤል ማስጠንቀቂያን፣ “በወራሪዎች የሚነዛ አጸያፊ የሥነ ልቡና ጦርነት” እንደኾነ ገልጾ፣ እያንዳንዱ ነዋሪ በየቤቱ እንዲቆይ መንገሩን፣ አሶሺዬትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

በአንጻሩ፣ በወታደራዊ የደኅንነት ማስጠንቀቂያው ስጋት የገባቸው የጋዛ ነዋሪዎች አካባቢውን ሲለቁ፣ ሌሎችም ከሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች በሚደርሷቸው ተፃራሪ ትዕዛዛት የተነሳ፣ ምን ማድረግ እንዳለባቸው፣ በተለይ ዛሬ ዐርብ ግራ ሲጋቡ መታየታቸው ተነግሯል፡፡

በጋዛ ከተማ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፍልስጥኤም ስደተኞች ኤጀንሲ ሓላፊ ኢናስ ሃምዳን፣ ለአሶሺዬትድ ፕሬስ እንደተናገሩት፣ “ይህ ትርምስ ነው፤ ማንም ምን ማድረግ እንዳለበት እየተረዳ አይደለም፤” ሲሉ፣ የነዋሪውን መደነጋገር ገልጸዋል፡፡ ሓላፊው ይህን ቢሉም፣ የድርጅቱ ሠራተኞች ሰሜናዊ ጋዛን እየለቀቁ እንደኾነ ተነግሯል፡፡

ከዛሬው ማስጠንቀቂያ አስቀድሞ፣ በጋዛ ውስጥ 340ሺሕ ነዋሪዎች እንደተፈናቀሉ፣ የመንግሥታቱ ድርጅቱ ገልጿል፡፡ እንዲህ ያለው የጅምላ መፈናቀል ሊያስከትል የሚችለው ሰብአዊ መዘዝ እንዳሳሰበው ያመለከተው ድርጅቱ፣ በቅርቡ እስራኤል ያካሔደችው ሙሉ ከበባ፣ የጋዛን አስከፊ የኑሮ ኹኔታ ከግምት መውሰድ እንደሚገባው አስገንዝቦ ነበር፡፡

በዙሪያ መለስ ከበባው፣ የጋዛ የኤሌክትሪክ፣ የውኃ እና የነዳጅ አቅርቦት በመቋረጡ፣ ፍልስጥኤማውያኑ እጥረት እያጋጠማቸው እንዳለ ተነግሯል፡፡ በዚኽም ጫና፣ በሐማስ ታግተው የተወሰዱ ታጋቾችን ለማስለቀቅ የምትጥረው እስራኤል፣ በምድር የምታካሒደው የእግረኛ ውጊያ ቅድመ ዝግጅት አካልም እንዳደረገችው ተመልክቷል፡፡

በጋዛ አቅራቢያ ያሉ ሲቪሎችን በመጠበቅ ረገድ ድክመቶች እንዳሉ፣ የእስራኤል ወታደራዊ አመራር አምኗል። ይኹንና፣ በአሁን ወቅት ትኩረቱ፣ በተከፈተበት ጦርነት ላይ እንደኾነ፣ በአጽንዖት ገልጿል።

የሐማስ ታጣቂዎች ቡድን በበኩሉ፣ እስራኤል ባለፉት 24 ሰዓታት ባካሔደቻቸው የአየር ጥቃቶች፣ 13 የእስራኤል እና የውጭ ታጋቾች እንደተገደሉ አስታውቋል፡፡ የእገታ ችግሩን ለመፍታት፣ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን፣ አሜሪካ እስራኤልን እንደምትደግፍ አረጋግጠዋል።

ከዚኹ ጋራ በተያያዘ በዲፕሎማሲው መስክ፣ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፥ ከዮርዳኖስ፣ ከእስራኤል እና ከሌሎች የባሕረ ሰላጤው ዐረብ ሀገራት መሪዎች ጋራ የተገናኙበትን ጉብኝት እያደረጉ ይገኛሉ። የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስትን ደግሞ፣ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ ለሚካሔዱ ስብሰባዎች እስራኤል ገብተዋል።

ቀውሱንና የሰብአዊ ጉዳቱን ለመቅረፍ፣ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት፣ በኹኔታው ላይ እየተወያየ እንደኾነ ተመልክቷል፡፡ የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ ኤል-ሲሲም፣ ዓለም አቀፍ ሰብአዊ ርዳታ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበው መረጋጋት እንዲሰፍን ጠይቀዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ጥረቶች በዚኽ መልኩ ቢቀጥሉም፣ የጋዛ ተጨባጭ ኹኔታ አሁንም አሳሳቢ ነው፤ ተብሏል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ሐማስን ትደግፋለች የምትባለው ኢራን፣ እስራኤል በጋዛ የምትወስደው ርምጃ፣ ከባድ መዘዝ እንደሚያስከትል አስጠንቅቃለች።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG