እስራኤል እና ሄዝቦላ ከዛሬ ረቡዕ ማለዳ ጀምሮ የተኩስ አቁም አድርገዋል። በሁለቱ መካከል የተደረሰው የተኩስ ማቆም በጋዛም ሌላ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈጸም መንገድ እንደሚከፍት የአሜሪካ እና የፈረንሳይ መሪዎች ተስፋ አድርገዋል።
የተኩስ አቁሙ ዜና እንደተሰማ በጦርነቱ ምክንያት ደቡባዊ ሌባኖስን ለቀው እንዲወጡ የተደረጉ ነዋሪዎች ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው በመኪና ሲተሙ ተስተውሏል።
የእስራኤል ሠራዊት ግን ሰዎች ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ወደ ተላለፈባቸው መንደሮች እንዳይመለሱ አሳስቧል።
አሜሪካ እና ፈረንሣይ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን ቁልፍ ሚና መጫወታቸው ሲነገር፣ የእስራኤል የፀጥታ ካቢኔም ትላንት ማምሻውን አጽድቆታል።
የአሜሪካው ፕሬዝደነት ጆ ባይደን ተኩስ ማቆሙ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን “ሁከት ለማስቆም ወሳኝ እርምጃ ነው” ብለዋል። የኢራን ተቀጥላ የሆኑት፣ ሌባኖስ የሚገኘው ሄዝቦላ እና ጋዛ የሚገኘው ሐማስ “ትልቅ ዋጋ ከፍለዋል” ሲሉ አክለዋል ባይደን።
ስምምነቱ “ቋሚ የተኩስ ማቆም እንዲሆን ተደርጎ የተነደፈ ነው” ብለዋል ባይደን። ሄዝቦላ እስራኤልን ማጥቃቱን ለማቆም በመስማማቱ “ሐማስ ግልጽ የሆነ አማራጭ ቀርቦለታል። ያለው ብቸኛ መውጫ መንገድ አሜሪካውያንን ጨምሮ ያገታቸውን ሰዎች መልቀቅ ነው” ሲሉ ተናግረዋል ባይደን።
በመጪዎቹ ቀናት አሜሪካ ከቱርክ፣ ግብጽ፣ ካታር፣ እስራኤል እና ከሌሎችም ጋራ በመሆን በጋዛ ተኩስ አቁም ላይ እንዲደረስ ግፊት እንደሚያደርጉ ባይደን ጠቁመዋል።
መድረክ / ፎረም