በጋዛ እና ሊባኖስ እየተካሄደ ያለው ጦርነት በሚቆምበት ሁኔታ ላይ ለመነጋገር በቀጠናው የሚገኙት የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ፣ ዛሬ ሐሙስ ከካታሩ መሪ ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ ጋራ ተገናኝተው ተወያይተዋል።
ብሊንከን በተጨማሪም ከካታሩ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሃመድ አል ታኒ ጋራ እንደሚገናኙ ታውቋል።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ብሊንከን ነገ ዓርብ በለንደን ከዓረብ ሃገራት ባለሥልጣናት ጋራ ስብሰባ እንደሚቀመጡም ታውቋል። ብሊንከን ከያዙት አጀንዳ ውስጥ ዋነኛው በጋዘ ለሚገኙ ፍልስጤማውያን የሚሰጠው ሰብዓዊ ዕርዳታ መጨመርን የሚመለከተው ነው፡፡
ፈረንሳይ በበኩሏ እስራኤል ከሄዝቦላ ጋራ ሊባኖስ ውስጥ በምታደርገው ውጊያ ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች የሚውል ገንዘብ ለማሰባሰብ ዛሬ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ አስተናግዳለች፡፡
ፈረንሣይ 108 ሚሊዮን ዶላር ቃል ስትገባ፣ ጀርመን በበኩሏ 103 ሚሊዮን ዶላር እንደምታዋጣ አስታውቃለች፡፡
በፓሪሱ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ በድምሩ 1 ቢሊዮን ዶላር ቃል እንደተገባ የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።
መድረክ / ፎረም