ኢራን በርካታ ሚሳዬሎችን ወደ እስራኤል ማስወጨፏን እስራኤል አስታውቃለች፡፡ ነዋሪዎች በቦምብ መጠለያ አካባቢ እንዲሆኑ የእስራኤል ሠራዊት ሲመክር፣ የአደጋ ማስጠንቀቂያ ጥሪ በመላ ሃገሪቱ ተሰምቷል።
ኢራን ባሊስቲክ ሚሳዬሎችን በቅርቡ ለማስወንጨፍ በመዘጋጀት ላይ ነች ሲሉ አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣን አስታውቀው ነበር።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት ባለሥልጣን እንዳሉት፣ ኢራን ጥቃቱን የምትፈጽም ከሆነ “አደገኛ ውጤት” ይኖረዋል።
እስራኤል ባለፈው ሳምንት የሄዝቦላ መሪን ሃሳን ናስራላህ እና ሌሎችንም መሪዎች እንዲሁም የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ምክትል አዛዥን መግደሏን ተከትሎ፣ በቀጠናው ውጥረት ጨምሯል።
የናሳራላህ ሞት መልስ ሳይሰጠው የሚቀር አይሆንም ስትል ኢራን ዝታለች፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የምድር ኃይሏን በመጠቀም በደቡብ ሊባኖስ በኢራን በሚደገፈው ሄዝቦላ ላይ የፈጸመችውን ወረራ ተከትሎ ከባድ ውጊያ መካሄዱን እስራኤል ዛሬ ማክሰኞ አስታውቃለች፡፡
ድንበር ዘለሉ ዘመቻ የተወሰነ ዒላማ ያለውና በተወሰነ ሥፍራ ያካሄደው እንደሆነ የገለፀው የእስራኤል ኃይል፣ በሰሜን እስራኤል ፀጥታን ለማምጣት የውጊያ ዘመቻው እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ሄዝቦላ እስራኤልን ለመውረር ዝግጅት ላይ ነበር ሲሉ የሠራዊቱ ቃል አቀባይ አስታውቀዋል።
መድረክ / ፎረም