በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሂዝቦላ በእስራኤል የተሽከርካሪ ቡድን ላይ አደጋ ጣለ


ፎቶ ፋይል፦ የእስራኤል ጥቃት በደቡባዊ ሊባኖስ ኪያም መንደር ሰማይ ላይ እአአ ሚያዚያ 17/2024
ፎቶ ፋይል፦ የእስራኤል ጥቃት በደቡባዊ ሊባኖስ ኪያም መንደር ሰማይ ላይ እአአ ሚያዚያ 17/2024

የሊባኖስ ታጣቂ ቡድን ሂዝቦላ፣ በአወዛጋቢው የደንበር አካባቢ፣ በእስራኤል ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ቡድን ላይ፣ ፀረ ታንክ ሚሳዬሎችንና መድፎችን በመተኮስ፣ አንድ እስራኤላዊ ሲቪል መግደሉን፣ ሂዝቦላ እና የእስራኤል ጦር፣ ዛሬ ዐርብ አስታወቁ፡፡

ሂዝቦላ እንደተናገረው፣ ትላንት ኀሙስ እኩለ ሌሊት ገደማ፣ ተዋጊዎቹ በወታደራዊ የተሽከርካሪ ቡድኑ ላይ ባደረሱት የደፈጣ ጥቃት፣ ሁለት ተሽከርካሪዎችን አውድመዋል፡፡

የእስራኤል ጦር በበኩሉ፣ የደፈጣ ጥቃቱ በመሠረተ ልማት ሥራዎች ላይ የነበረ አንድ እስራኤላዊ ሲቪል ማቁሰሉን ገልጾ፣ ግለሰቡ ከጉዳቱ የተነሣ ሕይወቱ ማለፉን አስታውቋል፡፡

በእስራኤል እና በሊባኖስ ደንበር ላይ የቆየው መጠነኛ ውጊያ፣ ከቅርብ ወራት ወዲህ እስራኤል ዋናውን የሂዝቦላ ታጣቂ ቡድን ዒላማ በማድረጓ፣ ወደ ሌሎችም አካባቢዎች ሊስፋፋ ይችላል፤ የሚል ስጋት ደቅኗል፡፡

በሁለቱም ሀገራት የደንበር አቅጣጫዎች በኩል፣ በዐሥር ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል።

በዚኹ ደንበር ተሻጋሪ ጦርነት በእስራኤል በኩል፣ 10 ያልታጠቁ ዜጎች እና 12 ወታደሮች ሲገደሉ፣ በሊባኖስ በኩል 50 ሲቪሎች እና 271 የሔዝቦላህ አባላትን ጨምሮ ከ350 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

በሌላ በኩል፣ ትላንት ኀሙስ፣ እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ደቡባዊ ራፋህ ከተማ ላይ ባደረሰችው የአየር ድብደባ፣ ቢያንስ አምስት ሰዎች መገደላቸውን፣ የፍልስጥኤም ሆስፒታል ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

2ነጥብ3 ሚሊዮን ከሚደርሰው የጋዛ ነዋሪ ከግማሽ በላይ የሚኾነው፣ እስራኤል የምድር ወረራ ልታደርግበት በተዘጋጀችውና በየቀኑ ሊባል በሚችል ደረጃ ጥቃት በምትሰነዝርበት ራፋህ ከተማ ውስጥ ተጠልሏል፡፡

የእስራኤል ጦር በአካባቢው ያከማቻቸው በርካታ ታንኮች እና ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች፣ ራፋህን ለመውረር የሚደረግ ዝግጅት ሒደት እንደሚመስል፣ የአሶሺዬትድ ፕሬስ ዘገባ አመልክቷል፡፡

በተያያዘ፣ በማዕከላዊ ጋዛ በተካሔደ የእስራኤል ታንክ ድብደባ አራት ሰዎች ተገድለዋል፡፡

እንዲሁም፣ በአደን ባሕረ ሰላጤ ላይ ሲጓዝ የነበረ አንድ መርከብ፣ በየመን ሁቲ ዐማፅያን፣ ትላንት ኀሙስ ጥቃት ደርሶበታል፡፡ የእስራኤልና ሐማስን ጦርነት ተከትሎ ከተሰነዘሩ የቡድኑ ጥቃቶች ይህ የቅርብ ጊዜው ነው፤ ተብሏል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የሐማስ ከፍተኛ የፖለቲካ ባለሥልጣን ለአሶሺዬትድ ፕሬስ እንደተናገሩት፣ እስላማዊው ታጣቂ ቡድን፣ ከእስራኤል ጋራ ለአምስት ዓመታትና ከዚያም በላይ የሚዘልቅ የእርቅ ስምምነት ለማድረግ ፈቃደኛ ነው።

ጦርነቱ የተጀመረው፣ ሐማስ እ.ኤ.አ. ጥቅምት 7 ቀን 1ሺሕ200 ሰዎችን የገደለበትንና 250 የሚኾኑትን አግቶ የወሰደበትን በእስራኤል ታይቶ የማያውቅ ደንበር ዘለል ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ነው።

እስራኤል፣ እስላማዊው ታጣቂ አሁንም 100 የሚደርሱ ታጋቾችንና ከ30 የሚበልጡ አስከሬኖችን በቁጥጥር ሥር እንዳዋሉ ነው፤ ብላለች፡፡

እንደ አካባቢው የጤና ባለሥልጣናት ገለጻ፣ ጦርነቱ እስከ አሁን ከ34ሺሕ በላይ ፍልስጥኤማውያንን ገድሏል፡፡ ከእነርሱም ሁለት ሦስተኛ የሚኾኑቱ ሕፃናት እና ሴቶች ናቸው፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG