እስራኤል እና ሐማስ ከሰባት ቀናት እፎይታ በኋላ ዛሬ ማለዳ እንደገና ውጊያ ቀጥለዋል። የእስራኤል መከላከያ ኃይል እንደሚለው፣ ውጊያው የቀጠለው ሐማስ የተኩስ ማቆም ስምምነቱን በመጣስ ሮኬት መተኮሱን ተከትሎ ነው።
ከጋዛ የተወነጨፈውን ሮኬት ኃይሉ ማክሸፉን በ X ማኅበራዊ መድረክ ላይ አስታውቋል።
በሐማስ የሚተዳደረው እና በጋዛ የሚገኘው የጤና ሚኒስቴር፣ በዛሬ ማለዳው ጥቃት ቢያንስ 32 ሰዎች እንደሞቱ አስታውቋል።
ለሮኬት ጥቃቱ ሐማስ ወዲያውኑ ሓላፊነት እንዳልወሰደ ታውቋል።
ለሰባት ቀናት ያህል የተደረገው የተኩስ ማቆም፣ በሐማስ በተወሰዱ ታጋቾች እና በእስራኤል ታሥረው በነበሩ ፍልስጤማውያን መካከል ልውውጥ እንዲኖር አስችሎ ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በአካባቢው የሚገኙት የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ ከእስራኤሉ ፕሬዝደንት አይሳክ ሄርዞግ ጋር ቴል አቪቭ ላይ ተገናኝተዋል። የተኩስ ማቆሙ ውጤት እያመጣ እንደነበር እና አሜሪካ እንዲቀጥል እንደምትሻ ብሊንከን ለሄርዞግ እንደናገሯቸው ተዘግቧል።
ብሊንከን በመቀጠልም ከፍልስጤም ራስ ገዝ ፕሬዝደንት ከሆኑትን ማህሙድ ሃባስ ጋር ራማላህ ላይ ተገናኝተዋል። በዌስት ባንክ የሚገኙ ፍልስጤማውያን ደህንነት እና ነፃነት የሚሻሻልበትን ሁኔታ ላይ መነጋገራቸውን ያአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ብሊንከን በመቀጠል ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በማቅናት፣ በዱባይ በሚካሄደው የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ በመሳተፍ ላይ ከሚገኙት የአረብ አገራት መሪዎች ጋር በጋዛ ጉዳይ ላይ እንደሚነጋገሩ ታውቋል።
መድረክ / ፎረም