የእስራኤል እና የሐማስ ታጣቂዎች ውጊያ ደቡባዊ ጋዛ ላይ ዛሬ ረቡዕ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡
ጦርነቱ መጠለያ እና የሰብአዊ ርዳታ ለማግኘት ተችግረው አጣብቂኝ ውስጥ በሚገኙት ፍልስጣኤማውያን ሲቪሎች ላይ ከባድ ጫና እየፈጠረ ነው ተብሏል።
የእስራኤል ጦር ትናንት ማክሰኞ በጋዛ ሰርጥ 250 በሚሆኑ ኢላማዎች ላይ የአየር ድብደባ ማካሄዱን ዛሬ ረቡዕ አስታውቋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከትናንት በስቲያ ሰኞ ከሰዐት በኋላ ጀምሮ እስራኤል ከከባድ የየብስ ጥቃት ጋር በጋዛ ላይ የምታደርገውን ከፍተኛ የቦምብ ድብደባ፣ የፍልስጤም ታጣቂዎችም እንዲሁ ወደ እስራኤል የሚተኩሱት ሮኬቶች መጨመራቸውን አመልክቷል።
የእስራኤል ወታደራዊ ባለስልጣናት ኃይሎቻቸው በጋዛ ሁለተኛ የሆነችውን ደቡባዊቷን ኻን ዮኒስ ከተማን እየከበቡ እንደሆነም ተነግረዋል፡፡
የእስራኤል የጦር ሠራዊት ባለፉት ቀናት ባወጣቸው ማስጠንቀቂያዎች የበርካታ የኻን ዩኒስ መንደሮች ነዋሪዎች ራቅ ወዳሉ የደቡብ ጋዛ አካባቢዎች እንዲሄዱ አሳስቦ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ግን በምዕራብ የሜዲትራኒያን ባህር፣ በደቡብ እና ምስራቅ ከግብፅ እና ከእስራኤል ጋር የሚያዋስነው ድንበር ስለተዘጋ ሰዎች የሚሄዱበት ቦታ እየጠበበ መሆኑ ተነግሯል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት በእስራኤል የተያዙ የፍልስጥኤም አካባቢዎች የሰብዓዊ ረድዔት አስተባባሪ ሊን ሃስቲንግስ ትናንት ባወጡት መግለጫ “ ጋዛ ውስጥ ደህንነቱ የተጠበቀ ምንም ቦታ የለም፣ የቀረ መሄጃም የለም” ብለዋል፡፡
መድረክ / ፎረም