የሐማስ መሪ ቴህራን ውስጥ መገደሉን ተከትሎ፤ ኢራን፣ በእስራኤል ላይ የበቀል እርምጃ እንዳትወስድና እንድትታቀብ በፈረንሣይ፣ ጀርመን እና እንግሊዝ ትላንት ሰኞ የቀረበውን ጥሪ ውድቅ አድርጋለች፡፡
የሶስቱ ሃገራት ጥያቄ “የፖለቲካ አመክንዮ የሌለውና ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋራ የሚቃረን ነው” ሲሉ የኢራኑ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ናስር ካናኒ ተናግረዋል።
ሶስቱ ሃገራት በጋዛ የሚካሄደውን ጦርነት እንዲሁም “ጦረኛ” ያሏትን እስራኤል እንዲያወግዙም ቃል አቀባዩ ጠይቀዋል።
ቃል አቀባዩ ”ጽዮናዊ አገዛዝ” ብለው የገለጿት እስራኤል ፈጸመችዉ ያሉትን ወንጀል ሶስቱ ሃገራት ሳይቃወሙ፣ “ኢራን ሉአላዊነቷና የግዛት አንድነቷ በተደፈረበት ሁኔታ ምላሽ እንዳትሰጥ ደፍረው ይጠይቃሉ” ሲሉ ተናግረዋል ናስር ካናኒ።
የሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣን ቴህራን ውስጥ በመገደሉ፣ ኢራን እስራኤልን የመበቀል መብት አላት ሲሉ የኢራኑ ፕሬዝደንት ትላንት ሰኞ ለእንግሊዙ ጠቅላይ ምኒስትር ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ እስራኤል እና አጋሮቿ ከኢራን ለሚሰነዘረው ጥቃት መዘጋጀት እንዳለባቸው የዋይት ሃውስ የብሔራዊ ደህንነት ም/ቤት ቃል አቀባይ ጃን ከርቢ አስጠንቅቀዋል። ጥቃቱ በዚህ ሳምንት ሊጀምር እንደሚችልም ተናግረዋል።
ውጥረቱ እያየለ ባለበት በዚህ ወቅት አሜሪካ ባሕር ሰርጓጅ እና አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቦቿን ወደ ቀጠናው አስጠግታለች፡፡ አሜሪካ መሣሪያዎቿን ወደ አካባቢው መላኳ ለኢራን መልዕክት ለማስተላለፍ መሆኑን የፔንታገን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
መድረክ / ፎረም