በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

እስራኤል በጋዛ የከፈተቸውን ወታደራዊ ጥቃት መቀጠሏ ተዘገበ


በእስራኤል እና በሃማስ መካከል በቀጠለው ግጭት የእስራኤል ወታደር በጋዛ ሰርጥ ወታደራዊ ዘመቻ ሲያደርግ ያሳያል። እአአ ሃምሌ 15/2024
በእስራኤል እና በሃማስ መካከል በቀጠለው ግጭት የእስራኤል ወታደር በጋዛ ሰርጥ ወታደራዊ ዘመቻ ሲያደርግ ያሳያል። እአአ ሃምሌ 15/2024

የእስራኤል ጦር ኃይል በጋዛ ሰርጥ የከፈተውን ወታደራዊ ዘመቻ በአየር እና በምድር በሚካሄዱ ጥቃቶች ቀጥሏል። በማዕከላዊ ጋዛ በሚገኘው የአል-ማጋዚ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ ያለ አንድ የመኖሪያ ቤት በእስራኤል የአየር ድብደባ መመታቱን ተከትሎ በጥቃቱ የተገደሉ አምስት ፍልስጤማውያንን አስከሬን ማግኘታቸውን የጋዛ የጤና አገልግሎት ባለስልጣናት አስታወቁ።

በአቅራቢያው የሚገኘው የ’ዴይር አል ባላህ’ ሆስፒታል ባለሥልጣናት በበኩላቸው ሦስት ሰዎች በአየር ድብደባው መገደላቸውን ተናግረዋል።

አሶሽየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ባጠናቀረው ሌላ ዘገባ መንገድ ላይ የነበረ አንድ ሰው መገደሉን እና ሌሎች ስድስት ሰዎች በአየር ድብደባው መቁሰላቸውን አመልክቷል። በሌላ በኩል እስራኤል በሶሪያ እና ሊባኖስ አዋሳኝ ድንበሮች አካባቢ በትላንትናው ዕለት በፈጸመችው የአየር ድብደባ ‘መሀመድ ባራ ካተርጂ’ የተባሉ ከፕሬዝዳንት በሽር አላሳድ እና ከአገዛዛቸው ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸው መሆኑ የተነገረ አንድ በንግድ ሥራውዎች የተሰማሩ ሰው ተገድለዋል። ዘገባዎች ጨምረው እንዳመለከቱት፣ ካተሪጂ የተገደሉት ሁለቱን አገሮች ከሚያዋስነው የድንበሩ አካባቢ ካለ አውራ ጎዳና ላይ የተሳፈሩበት መኪና በተመታበት ወቅት ነው።

ካተርጂ በነዳጅ ሽያጭ ሥራ የተሰማሩ ባለሀብት ሲሆኑ፤ በአሳድ መንግስት እና በእስላማዊው ጽንፈኛ ቡድን መካከል የሚደረጉ የንግድ ሽርክናዎችን የማቀላጠፍ ሥራ ይሰራሉ’ በሚል በምትወነጅላቸው ዩናይትድ ስቴትስ ከዚህ ቀደም ማዕቀብ ተጥሎባቸው ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል ባለፈው ቅዳሜ ያካሄደችው የአየር ድብደባ ኢላማ እንደ ነበር የተነገረው የሃማስ ወታደራዊ መሪ እጣ እስካሁን አልታወቀም።

እስራኤል ካሁን ቀደም በጦርነቱ ለተፈናቀሉ በርካታ ፍልስጤማውያን ደህንነት የተሻለ ቀጠና ነው’ ብላ ከነበረው ካን ዮኒስ ወጣ ብላ በምትገኘው አል-ማሳዊ ላይ በፈጸመችው የአየር ድብደባ 90 የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው የጤና ባለስልጣናት ተናግረዋል።

እስራኤል በበኩሏ ጥቃቱ 1 ሺሕ 200 ሰዎችን የተገደሉበትን እና ሌሎች 250 ሰዎች የታገቱበትን፤ ሃማስ ባለፈው የመስከረም ወር መገባደጂያ በደቡባዊ እስራኤል የፈጸመውን ጥቃት ባቀነባበረው መሐመድ ዲፍ ላይ የተነጣጠረ መሆኑን አመልክታለች።

የሃማሱን ጥቃት መነሻ በማድረግ እስራኤል በጋዛ በከፈተችው ወታደራዊ ዘመቻ እስካሁን ቁጥራቸው ከ38 ሺሕ 500 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ሲገደሉ ከ88 ሺሕ 800 በላይ የሚሆኑ ሌሎሽ መቁሰላቸውን በሃማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቋል።

ግብፅ፣ ኳታር እና ዩናይትድ ስቴትስ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረግ ሲጥሩ ቢቆዩም፤ ጦርነቱ እንዲቆም እና ጋዛ ውስጥ በሃማስ ተይዘው የሚገኙትን ታጋቾችን መለቀቅ ካካተተ አዲስ ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG