በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

እስራኤል በማዕከላዊ ጋዛ አዲስ የአየር ጥቃት አደረሰች


የእስራኤል ወታደራዊ ኅይሎች በማዕከላዊ ጋዛ ባደረሱት የቦምብ ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸው አዛውንት በካን ዩንስ ከሚገኘው ናስር ሆስፒታል እአአ ሐምሌ 9/2024
የእስራኤል ወታደራዊ ኅይሎች በማዕከላዊ ጋዛ ባደረሱት የቦምብ ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸው አዛውንት በካን ዩንስ ከሚገኘው ናስር ሆስፒታል እአአ ሐምሌ 9/2024

የእስራኤል ወታደራዊ ኅይሎች ዛሬ ረቡዕ ማዕከላዊ ጋዛን ማጥቃታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ትላንት ማክሰኞ ወደፍልስጥኤማዊያን ተፈናቃዮች መጠለያነት በተቀየረ ትምሕርት ቤት ላይ ባደረሱት የአየር ድብደባ ሃያ ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውን የፍልስጥኤም የጤና ባለስልጣናት ተናግረዋል፡፡

የእስራኤል የጦር ኅይል እአአ ጥቅምት ሰባት ቀን ደቡባዊ እስራኤል ላይ ሃማስ ባደረሰው ህይወት ያጠፋ ጥቃት የተሳተፈ ታጣቂ ዒላማ ያደረገ ጥቃት እንደነበር ተናግሯል፡፡ የጦር ኅይሉ በአየር ጥቃቱ ሲቪሎች እንደተገደሉ ያመለከቱትን ሪፖርቶች በመመርመር ላይ መሆኑንም ባለስልጣናቱ ገልጸዋል፡፡

ትላንት ማክሰኞ ሃማስ ጥቃቶቹ የተኩስ አቁም ድርድሩን ሊጎዱ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ በበኩሉ ጥቃቱን እስራኤል ሲቪሎች አካባቢዎችን ለቅቀው እንዲወጡ ያስተላለፈችውን ትዕዛዝ በሚመለከት ያለውን ስጋት ገልጿል፡፡

እስራኤል ባለፈው ዕሁድ ሲቪሎች ወደምዕራባዊው የጋዛ ከተማ አካባቢ እንዲሄዱ ካዘዘች በኋላ የመከላከያ ኅይሎቿ በነዚያው መተላለፊያዎች ላይ ከባድ ድብደባ ማድረሳቸውን የተመዱ የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ ተናግሯል፡፡

በተያያዘ ዜና ጄኔቫ ላይ የተሰበሰቡት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሞያዎች ባወጡት መግለጫ በጋዛ ሰርጥ የረሃብ ቸነፈር እየተስፋፋ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በእስራኤል እና በሃማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ በቀጠለው ጥረት የግብጽ የእስራኤል እና የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ የደሕንነት ባለስልጣናት ዛሬ ረቡዕ ካታር ላይ እንደሚሰበሰቡ የተለያዩ የዜና ማሰራጫዎች ዘግበዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG