የሃማስ መሪዎች በሁለቱ ወገኖች መሃከል እየተካሄደ ያለውን የተኩስ አቁም ድርድር ሊጎዳው እንደሚችል ቢያስጠነቅቁም፤ የእስራኤል ጦር ግን በጋዛ ከተማ የጀመረውን ወታደራዊ ዘመቻ በዛሬው ዕለት አጠናክሮ ቀጥሏል። የእስራኤል ወታደራዊ ኃይሎች ‘በሸጃያ አካባቢ ባካሄዱት ውጊያ በርከት ያሉ ታጣቂዎችን ገድለናል’ ብለዋል።
ይሁን እንጂ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ቢሮ እስራኤል በከተማይቱ ላይ የከፈተችው ወታደራዊ ዘመቻ እና ሲቪሎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ የሰጠችው ትዕዛዝ ያሳደሩበትን ሥጋት ገልጿል። የመንግሥታቱ ድርጅት አክሎም እስራኤል የሰላማዊ ዜጎች ደህንነት መጠበቁን ለማረጋገጥ፤ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው ወደ ምዕራባዊ የጋዛ ከተማ እንዲሄዱ ባለፈው እሁድ የሰጠችው ትዕዛዝ የእስራኤል ጦር በአካባቢው የያካሂደውን ወታደራዊ ዘመቻ ከዚያ በኋላ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጾ እንደ ነበር አስታውሷል።
"የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ጽ/ቤት የእስራኤል ጦር ሰላማዊ ሰዎች አካባቢዎቹን ለቀው እንዲወጡ በሚል የሚሰጣቸው ትዕዛዞች አንዳንዴ ነዋሪዎች ወታደራዊ እንቅስቃሴዎቹ ወደሚካሄዱባቸው አካባቢዎቹ እንዲዛወሩ ማድረጋቸውን ጨምሮ ግራ የሚያጋቡ መሆናቸውን ጠቅሶ በተደጋጋሚ ሥጋቱን ገልጿል። አሁንም እስራኤል ጋዛ ውስጥ የሚገኙ ሲቪሎችን ደህንነት ለማረጋገጥ አስፈላጊውን ጥረቶች በሙሉ እንድታደርግ በድጋሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን” ሲል ድርጅቱ በመግለጫው አሳስቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የግብጻውያን አደራዳሪዎች ለጋዛው ጦርነት እልባት ለማበጀት በያዙት እና ረጅም ጊዜ ባስቆው ጥረት ቀጥለዋል። በተያያዘ በእስራኤል እና በሃማስ መሃከል የተኩስ አቁም ሥምምነት እንዲደረስ ከተያዘው ጥረት ጋር በተዛመደ የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ግብፅ እንደሚገኙ ዋይት ሃውስ አስታውቋል።
የዋይት ሃውስ የብሄራዊ ደህንነት ጉዳዮች ቃል አቀባይ ጃን ኪርቢ በትላንትናው ዕለት ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፤ ‘የሲአይኤ ድሬክተር ቢል በርንስ እና የዩናይትድ ስቴትስ የመካከለኛው ምስራቅ መልዕክተኛ ብሬት ማክገርክ ከግብፅ፣ ከእስራኤል እና ከዮርዳኖስ አቻዎቻቸው ጋር ለመነጋገር ካይሮ ይገኛሉ’ ብለዋል።
"በሁለቱ ወገኖች መካከል ሥምምነት ለመድረስ አሁንም መሞላት የሚሹ አንዳንድ ክፍተቶች አሉ” ያሉት ኪርቢ፤ “ሆኖም ለስኬት ሊያበቃ የሚችል እድል መኖሩን ባናምን ቡድኑን ወደዚያ ባልላክን ነበር" ብለዋል።
መድረክ / ፎረም