በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩናይትድ ስቴትስ ለጋዛ ተኩስ አቁም ዕቅድ ተጨማሪ ድጋፍ ለማሰባሰብ ጥረት ይዛለች


በጥቃት የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን በራፋ፣ ጋዛ ሰርጥ እአአ የካቲት 27/2024
በጥቃት የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን በራፋ፣ ጋዛ ሰርጥ እአአ የካቲት 27/2024

የጋዛ ጦርነት በጊዜያዊነት እንዲገታ፥ የሰብዓዊ ረድዔት አቅርቦቱም እንዲጨምር እንዲሁም ሐማስ ታጋቾቹን እንዲለቅ የቀረበው የተኩስ አቁም ሀሳብ ዛሬም ዕጣ ፈንታው አልለየም። ሃማስ ለቀረበው ሃሳብ እስካሁን መልስ ያልሰጠ ሲሆን የእስራኤል ባለስልጣናት በአንዳንዶቹ የተኩስ አቁም እቅዱ ዝርዝሮች ላይ ጥያቄ አንስተዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ ዕቅዱ ተቀባይነት አግኝቶ በሥራ ላይ ይውል ዘንድ የተመድ የጸጥታ ምክር ቤትን ዕገዛ በመጠየቅ ላይ ነች።

ቪኦኤ ያነበበው የዩናይትድ ስቴትስ ረቂቅ ውሳኔ ሀማስ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ባስቸኳይ ያለቅድመ ሁኔታ ተቀብሎ ተግባራዊ እንዲያደርግ ይጠይቃል።

ስምምነቱ በአፋጣኝ ሥራ ላይ ከዋለ ተኩስ እንዲቆም እና የእስራኤል ኃይሎች በጋዛ የህዝብ መኖሪያ አካባቢዎች እንዲወጡ ታጋቾች እንዲለቀቁ የሚያደርግ መሆኑ በረቂቅ ውሳኔው ተመልክቷል። ከዚህም ሌላ ሰብዓዊ እርዳታው እንዲያድግ እና መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲቀጥሉ እና ፍልስጥኤማዊያን ስደተኞች ወደመኖሪያቸው እንዲመለሱ የሚያደርግ መሆኑን ረቂቅ ውሳኔው ያሳያል።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር ትላንት ሰኞ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል የተኩስ አቁም ዕቅዱ ባለፈው ሀሙስ ለሃማስ የቀረበለት መሆኑን ገልጸው ገና መልስ እንዳልሰጠ አስታውቀዋል። "በዕቅዱ ውስጥ የተካተቱት አበይት ነጥቦች ከበርካታ ሳምንታት በፊት ሃማስ ካቀረበው ሃሳብ ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ ተመሳሳይ ነው" ሲሉም አክለዋል።

በቀረበው እቅድ ውጊያው ለስድስት ሳምንታት እንዲገታ፥ አንዳንዶች ታጋቾች እንዲለቀቁ፥ በየቀኑ 600 እርዳታ የጫኑ መኪናዎች ለፍልስጥ ኤማውያን እንዲደርሱ እና ተኩሱ በዘላቂነት እንዲቆም የሚያደርግ

ቀጣይ ድርድር እንዲካሄድ የሚሉት መሠረታዊ ዝርዝሮች ተካትተውበታል። ትላንት ሰኞ የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት ሲናገሩ የተኩስ አቁም ሃሳቡን ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ባለፈው ሳምንት በይፋ ቢያቀርቡትም የእስራኤል የተኩስ አቁም ሃሳብ መሆኑን በአጽንዖት ተናግረዋል።

የኋይት ሐውስ የብሔራዊ ጸጥታ ጉዳዮች ቃል አቀባይ ጃን ከርቢ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል ከአሁን ቀደም ባለስልጣናት ድርድሮች እንዳይሰናከሉ በመስጋት በይፋ ለመናገር ፈቃደኛ እንዳልነበሩ አስታውሰው አሁን በይፋ መነገሩ የእስራኤል ባለስልጣናት ላይ ጫና ለማሳደር ሳይሆን ተብሎ ሳይሆን ከሆነም ሀማስ እና መሪዎቹን ለመጫን ነው" ብለዋል። ቀደም ሲል ጃን ከርቢ ሃማስ የተኩስ አቁም ሃሳቡን ከተቀበለ እስራኤል እንደምትቀበል ተናግረው ነበር።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ትላንት ሀገራቸው ለምክር ቤታዊ ኮሚቴ ባደረጉት ንግግር " ያቀረብናቸው ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ በከኩስ አቁም ሃሳቡ ተስማምተዋል መባሉ ስህተት ነው" ማለታቸውን ከጽህፈት ቤታቸው የወጣው መግለጫ አመልክቷል።

በኢንዱስትሪ የበለጸጉት የቡድን ሰባት አባል ሀገሮች ትላንት ሰኞ ባወጡት የጋራ መግለጫ የቀረበውን የተኩስ አቁም ዕቅድ ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፉት አስታውቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ትላንት ሰኞ በኢንተርኔት በርቀት የተሰበሰቡት የግብጽ፥ የዮርዳኖስ፥ የሳውዲት አረቢያ፥ የካታር እና የተባበሩት የአረብ ኤሚሬቶች ዘላቂ የተኩስ አቁም ድርድር እንዲደረግ የተያዘውን ጥረት እንደሚደግፉ አስታውቀዋል። በፕሬዚደንት ባይደን የቀረበውን የተኩስ አቁም ዕቅድ ከልብ አዎንታዊ በሆነ መልኩ ማጤንም አስፈላጊ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተው አሳስበዋል።

በተያያዘ ዜና በጋዛ በተለይም ሰሜናዊ እና ደቡባዊ ጋዛ የቀጠለው ውጊያ ለፍልስጥኤማዊያኑ እጅግ አጣዳፊ የሆነውን ሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ የባሰ አዳጋች እያደረገው መሆኑን የተ መ ድ የሰብዓዊ ረድዔት ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG