በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ በኩል የሚገኘውን የራፋ መተላለፊያ ተቆጣጠሩ፣ ራፋን በአየር ደበደቡ


የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ ሰርጥ ድንበር አቅራቢያ በደቡብ እስራኤል፣ እአአ ግንቦት 7/2024
የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ ሰርጥ ድንበር አቅራቢያ በደቡብ እስራኤል፣ እአአ ግንቦት 7/2024

የእስራኤል ጦር ሠራዊት በዛሬው ዕለት በጋዛ ሰርጥ እና በግብፅ መካከል የሚገኘውን፣ በጋዛ በኩል ያለውን የራፋ መተላለፊያ መቆጣጠሩን ይፋ አድርጓል። ጦሩ ይህን ያደረገው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ካዘዘ እና ተደጋጋሚ የአየር ድብደባ ከአካሄደ አንድ ቀን በኋላ ነው።

የአሁኑ የእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ የተከፈተው የእስራኤል ባለሥልጣናት ሃማስን ድል ለመንሳት ለያዙት አላማ በራፋህ ላይ የሚያካሂዱት ወታደራዊ ዘመቻ እንደሚያስፈልጋቸው ለሳምንታት ሲናገሩ ከሰነበቱ በኋላ ነው። ዩናይትድ ስቴትስ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ሌሎች በአንጻሩ በሰላማዊ ሰዎች በተጨናነቀው በዚህ አካባቢ ጥቃት መክፈቱ ‘ሰብአዊ እልቂት ሊያስከትል ይችላል’ ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል በበኩላቸው ዛሬ ማክሰኞ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት ‘ዳግም የበዛ እልቂት ያስከትላል’ የሚል ሥጋት አድሮብኛል። ምንም ይበሉ ምን በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት የሚያደርስ ነው" ብለዋል። ጋዛ ውስጥ አንዳችም ከአደጋ የነጻ ሥፍራ ያለመኖሩንም አያይዘው አመልክተዋል።

ረሃብ ሰሜናዊ ጋዛ ላይ እያንዣበበ ባለበት ባሁኑ ወቅት ራፋ ላይ ጥቃት መክፈት “ብርቱ ስህተት” ነው ያሉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽም “ፖለቲካዊ ጉዳት እና ሰብአዊ ቀውስ የሚያስከትል ነው” ብለውታል። "ሰላም ለማምጣት ለሳምንታት ሲካሄድ የቆየው ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የተኩስ አቁም እና የታጋቾችን መለቀቅ በማስገኘት ፋንታ አውዳሚ ጥቃት ራፋ ላይ መክፈት እጅግ አሳዛኝ ነው የሚሆነው’ ሲሉም በመንግሥታት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል። የእርዳታ ቁሳቁስ ወደ ጋዛ የሚገባባቸው ሁለቱ ዋና ዋና መተላለፊያዎች - ራፋ እና ከረም ሻሎም - ‘በአስቸኳይ መከፈት አለባቸው’ ሲሉም አሳስበዋል።

የዮርዳኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው ኤክስ በተሰኘው የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ባሰፈሩት አስተያየት እስራኤል ለድርድር እድል ከመስጠት ይልቅ የራፋ መተላለፊያ መቆጣጠር እና የሰብአዊ እርዳታ መተላለፊያዎችን ዘጋች’ ሲሉ ወቅሰዋል። አያይዘውም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት “አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ” ሲሉ ጥሪ አሰምተዋል። “የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ተጠያቂ መሆን አለባቸው” ሲሉም አክለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤሉ መከላከያ ሚንስትር ዮአቭ ጋላንት-‘ሃማስ እስኪደመሰስ አለያም የመጀመሪያው ታጋች እስኪመለስ ድረስ በራፋ የሚካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ይቀጥላል’ ማለታቸው ተዘግቧል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG