በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

እስራኤል ሊባኖስ ውስጥ የሄዝቦላ ተዋጊዎችን ገደለች


የእስራኤል ጥቃት በደቡባዊ ሊባኖስ ኪያም መንደር ሰማይ ላይ እአአ ሚያዚያ 17/2024
የእስራኤል ጥቃት በደቡባዊ ሊባኖስ ኪያም መንደር ሰማይ ላይ እአአ ሚያዚያ 17/2024

የእስራኤል የጦር ኃይል በመላዋ ጋዛ ሰርጥ የሀማስ ታጣቂዎችን እና የቡድኑን ይዞታዎች ኢላማ ያደረጉ የአየር ድብደባዎች ማካሄዱን ትናንት ሀሙስ አስታወቀ። ደቡባዊ ሊባኖስ ላይ ባካሄደው የአየር ጥቃት ደግሞ ሁለት የሄዝቦላ ታጣቂዎችን መግደሉን አስታውቋል።

ሊባኖስ ላይ የተካሄደው የአየር ጥቃት ሰሞኑን በእስራኤል እና በሄዝቦላ መካከል እየተካሄደ ካለው ድንበር ተሻጋሪ ውጊያ የቀጠለ ሲሆን የእስራኤል እና ሃማስ ጦርነት ከጋዛ አልፎ እየተስፋፋ ነው የሚል ስጋት ቀስቅሷል።

አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው ሄዝቦላ እስራኤል ኪፋር ኪላ በተባለ አካባቢ ባደረሰችው የአየር ድብደባ ሁለት ተዋጊዎቼ ተገድለውብኛል ብሏል። እስራኤል በበኩሏ ሄዝቦላ ሰሜናዊ ግዛቷ ላይ ባደረሰው ጥቃት 14 ወታደሮቼ ቆስለውብኛል ማለቷን ኤኤፍፒ ጠቅሷል።

ይህ በዚህ እንዳለ ኋይት ሐውስ ቤተ መንግሥት እንዳስታወቀው የዩናይትድ ስቴትስ እና የእስራኤል ባለስልጣናት እስራኤል ደቡባዊ ጋዛ ራፋህ ላይ ወታደራዊ ጥቃት ለማካሄድ ያላት ዕቅድ ዩናይትድ ስቴትስ ዘንድ የፈጠረውን ስጋት በተመለከተ ትናንት ሀሙስ ተወያይተውበታል።

ሁለቱም ወገኖች ራፋህ ላይ ሃማስ ድል መመታት እንዳለበት ሁለቱም ወገኖች የተስማሙበት መሆኑን የገለጸው ኋይት ሀውስ የዩናይትድ ስቴትስ የውይይቱ ተሳታፊዎች ራፋህ ላይ ስለሚወሰዱ የተለያዩ እርምጃዎች ያላቸውን ስጋት መግለጻቸውን ጠቁሟል። የእስራኤል ተወያዮችም ስጋቱን ሊያጤኑት መስማማታቸውን አመልክቷል።

ይህ በዚህ እንዳለ የዓለም የምግብ ፕሮግራም በዚህ ሳምንት ለጋዛ 374 ቶን ስንዴ ማስገባቱን አስታውቋል። የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች ትናንት ሀሙስ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል ጋዛ ውስጥ የተደቀነውን የረሃብ ቸነፈር ለመከላከል የሚቻለው በየቀኑ የምግብ አቅርቦት ማስገባት ከተቻለ ብቻ መሆኑን አሳስበዋል። የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ በበኩላቸው እስራኤል የእርዳታ ተደራሽነቱን ለማሻሻል ቃል ብትገባም ምንም ያህል ውጤታማ አልሆነም ብለዋል።

በሌላ ዜና ትናንት በጸጥታ ምክር ቤት ዩናይትድ ስቴትስ ድምጽን በመሻር ስልጣኗ ተጠቅማ የመንግሥታቱ ድርጅት ፍልስጥኤምን ሙሉ አባል አድርጎ እንዳይቀበል ተከላክላለች። እንግሊዝ እና ስዊዘርላንድ ድምጸ ተአቅቦ ያደረጉ ሲሆን የተቀሩት 12 የምክር ቤቱ አባላት የቀረበውን ውሳኔ ደግፈዋል።

በመንግሥታቱ ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ከትናንት በስተያ ረቡዕ በደቡብ ኮሪያ ጉብኝታቸው ላይ በሰጡት ቃል ዩናይትድ ስቴትስ የቀረበውን ውሳኔ የእስራኤል እና ፍልስጥኤማዊያንን ግጭት ጎን ለጎን ሁለት ሀገር በመመስረት መፍታት የሚለው ሃሳብ አድርጋ እንደማታየው ገልጸዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG