በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አዲሱን የተኩስ አቁም ሃሳብ እያጤኑ ያሉት እስራኤል እና ሐማስ ውጊያውን ቀጥለዋል


በደቡባዊ ጋዛ ሰርጥ የምትገኘው ኻን ዩኒስ በቦምብ ጥቃት ከደረሰ በኋላ በህንፃዎች ላይ ጭስ ሲወጣ ይታያል፤ እአአ የካቲት 1/2024
በደቡባዊ ጋዛ ሰርጥ የምትገኘው ኻን ዩኒስ በቦምብ ጥቃት ከደረሰ በኋላ በህንፃዎች ላይ ጭስ ሲወጣ ይታያል፤ እአአ የካቲት 1/2024

እስራኤል ወታደሮቿ በጋዛ ሰርጥ ከሐማስ ታጣቂዎች ጋር መዋጋታቸውን አስታወቀች፡፡ ማዕከላዊ እና ሰሜናዊ ጋዛ ውስጥ ብዛት ያላቸው የሐማስ ተዋጊዎችን መግደሏንም ተናግራለች፡፡ እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ ሰርጥ የምትገኘው ኻን ዩኒስ ላይ የአየር ጥቃት ማደረሷም ተዘግቧል፡፡

እስራኤል እና ሐማስ ውጊያውን የቀጠሉት ሁለቱን ወገኖች በቀረበላቸው አዲስ የተኩስ አቁም ሃሳብ እንዲስማሙ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ያሉት አደራዳሪዎች ምላሻቸውን ለመስማት እየጠበቁ ባሉበት በዚህ ወቅት ነው፡፡ የቀረበው የተኩስ አቁም ሀሳብ ውጊያው ለአጭር ጊዜ እንዲቆም እና በሐማስ ቁጥጥር ሥር ያሉትን ታጋቾች ለማስለቀቅ የታለመ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የተኩስ አቁም ሃሳቡ የቀረበው በሳምንቱ መጀመሪያ የዩናይትድ ስቴትስ፣ የካታር፣ የእስራኤል እና የግብጽ ባለሥልጣናት ፓሪስ ላይ ባደረጉት ውይይት ሲሆን የሐማስ መሪ ኢስማኤል ሐኒዬ በተኩስ አቁሙ ጉዳይ ለመነጋገር ወደ ካይሮ እንደሚጓዙ ተጠብቆ ነበር፡፡

ስለአዲሱ የተኩስ አቁም ሓሳብ ዝርዝር ይዘት ትናንት ረቡዕ የተጠየቁት የኋይት ሐውስ የብሔራዊ ጸጥታ ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጃን ከርቢ የይዘቱ ዝርዝር የመጨረሻ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው ስምምነቱ ከተቋጨ በኋላ ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ያም ቢሆን በጥቅሉ ዓላማው በህዳር ወር ከተደረሰው እና ለአንድ ሳምንት ያህል ከቆየው ተኩስ አቁም ረዘም ላለ ጊዜ እንዲዘልቅ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ረድዔት ጉዳዮች አስተባባሪ ቢሮ ኅላፊው ማርቲን ግሪፊትዝ ከጋዛ ነዋሪ ህዝብ ሰባ አምስት ከመቶ የሚሆነው ከቀየው መፈናቀሉን ትናንት ረቡዕ ለመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት የገለጹ ሲሆን ተፈናቃዮቹ የሚኖሩት በየቀኑ እየተባባሰ በሚሄድ እጅግ አስከፊ ሁኔታ ውስጥ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ ክግብጽ እና ከእስራኤል ለተፈናቃዮቹ እርዳታ ማስገቢያ እና ሲቪሎች የሚንቀሳቀሱባቸው በርካታ መንገዶች እንዲከፈቱ ተማጽኖ አቅርበዋል፡፡

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪው ጥሪውን ያሰሙት ብዛት ያላቸው የመንግሥታቱ ድርጅት የፍልስጥኤማውያን ረድዔት መስሪያ ቤት (ኡንርዋ) ሠራተኞች እ አ አ ጥቅምት 7 ቀን በተፈጸመው የሽብርተኛ ጥቃት ሳይካፈሉ አልቀሩም የሚል ውንጀላ ማቅረቧን ተከትሎ ዋና ዋና ለጋሾች ለተቋሙ የሚሰጡትን እርዳታ ባቋረጡበት በአሁኑ ወቅት መሆኑ ነው፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG