አንድ ቁልፍ የተባሉ የሄዝቦላ አዛዥ በእስራኤል የአየር ጥቃት ዛሬ ደቡብ ሌባኖስ ውስጥ መገደላቸው ታውቋል።
ዊሳም አል ታዊል የተባሉት አዛዥ የተገደሉት በመኪናቸው ውስጥ ሆነው ከእስራኤል ጋር በሚዋሰነው አካባቢ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር አንድ የሌባኖስ የፀጥታ ባለሥልጣን አስታውቀዋል።
እስራኤል ዛሬ ሰኞ በሄዝቦላ ኢላማዎች ላይ ጥቃት መፈፀሟን ብታስታውቅም፣ ስለ አዛዡ ግድያ ግን ያለችው የለም።
ዊሳም አል ታዊል ከእስራኤል እና ሐማስ ጦርነት ወዲህ የተገደሉ ከፍተኛ የሄዝቦላ አዛዥ መሆናቸው ታውቋል።
በሌባኖስ እና እስራኤል ድንበር አካባቢ በተፈጸሙ ጥቃቶች 135 የሚሆኑ የሄዝቦላ ተዋጊዎችን ጨምሮ 180 ሰዎች ሲገደሉ፣ ሶስት ጋዜጠኞችና ሌሎች 17 ሲቪሎችም ሕይወታቸውን አጥተዋል።
እስራኤል ዛሬ ሰኞ በማዕከላዊ እና ደቡብ ጋዛ አዲስ ጥቃት እንደፈጸመች አስታውቃለች፡፡
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ነታንያሁ ትናንት እሁድ ለካቢኔያቸው ባደረግጉት ንግግር፣ ጥቃቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
መድረክ / ፎረም