በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኔታኒያሁ እንደገና ዛቱ


ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ

እሥራኤል ሁሉንም ዓላማዎች እስክታሳካ ጦርነቱ እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ መዛታቸውን ተከትሎ ጦራቸው ዛሬ (ማክሰኞ)ጋዛ ሰርጥ ውስጥ አዲስ የአየር ድብደባ ፈፅሟል።

የሐማስ ታጣቂዎች ጥቃት ለማድረስ ይጠቀሙበታል ያላቸውን የመሽለኩለኪያ ዋሻዎችና ቦታዎችን ጨምሮ ከመቶ በላይ ዒላማዎችን ማጥቃቱን የእሥራኤል ጦር አስታውቋል።

በማዕከላዊ ጋዛ ውስጥ በሚገኙት ኑሴይራት፣ ማጋዚ እና ቡሬጅ የስደተኞች መጠለያ አካባቢዎች በአየርና በከባድ መሣሪያ መመታታቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ኔታንያሁ ለሊኩድ ፓርቲያቸው አባላት ትናንት በሰጡት አስተያየት “በታጣቂው ቡድን የተያዙ ቀሪ ታጋቾችን ለማስፈታት ከተፈለገ እሥራኤል በሐማስ ላይ ወታደራዊ ጫናዋን ማበርታት አለባት” ብለዋል።

ኔታኒያሁ "በመጭዎቹ ቀናት ውጊያውን እናሰፋለን፤ ጦርነቱ ረጅም ነው፤ እንዲህ ፈጥኖ አይቆምም” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዎል ስትሪት ጆርናል አስተያየት አምድ ላይ ባሠፈሩት የመንግሥታቸው አቋም “ሐማስ መጥፋት አለበት፤ ጋዛ ሰርጥ ከወታደራዊ ኃይል ነፃ መሆን እንዲሁም የፍልስጥዔማዊያን ሁሉ ከፅንፈኛነት መላቀቅ አለባቸው” ብለዋል።

ከምድር ጦር ሌላ በሺሆች የሚቆጠሩ የአየር ላይ ጥቃቶችን ያካተተው የእሥራኤል ዘመቻ አብዛኛውን የጋዛ ክፍል ያፈራረሰ ሲሆን በጦርነቱ ከ20 ሺህ 400 በላይ ፍልስጥዔማዊያን መገደላቸውን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በጦርነቱ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ 2.3 ሚሊየን ሰዎችም ደቡብ ጋዛ ውስጥ እጅግ በተጨናነቁ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ እንደሚገኙ ተገልጿል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG