የሐማስ ከፍተኛ መሪ ኢስማኢል ሃኒዬህ በጋዛ ስላለው ጦርነት ከግብፅ ባለሥልጣናት ጋር ለመምከር ዛሬ ረቡዕ ካይሮ ይገኛሉ ብሏል።
ግብፅ፤ ቀደም ሲል በህዳር ወር መጨረሻ ላይ፣ በታጣቂ ቡድኑ የታገቱ ከ100 በላይ ሰዎችን ማስፈታትን ጨምሮ ለሳምንት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት በማስፈጸም በሐማስ እና በእስራኤል መካከል የሽምግልና ሚና ተጫውታለች፡፡
ሐማስ በርካታ ታጋቾችን እንዲለቅ የሚያካትተውን አዲስ የተኩስ አቁም ስንምምነት አስመልክቶ ድርድሮች ቢካሄዱም፣ ተፋላሚዎቹ ወገኖች ስምምነት ላይ አልደረሱም።
የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ፣ እስራኤል ታጋቾቹን ለማስለቀቅ ተጨማሪ ሰብዓዊ የተኩስ አቁም ፋታ ለማድረግ መዘጋጀቷን፣ ትናንት ማክሰኞ ለዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች ስብስብ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ አክለውም እስራኤል የፍልስጤም ህዝብን ሳይሆን ሃማስን ብቻ ነው የምትዋጋው ብለዋል።
ውጊያው ዛሬ ረቡዕ በጋዛ የቀጠለ ሲሆን፣ የእስራኤል ጦር ከ300 በላይ ኢላማዎችን ማጥቃት መቻሉን ተናግሯል፡፡
በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት፤ የምግብ ፣ የውሃ እና የመድኃኒት አቅርቦት ለሚያስፈልጋቸው የጋዛ ነዋሪዎች፣ የተፋጠነ የርዳታ አቅርቦትን ለማመቻቸት፣ ውጊያው ለአፍታ እንዲቆም የሚጠይቅ ውሳኔ ላይ፣ ዛሬ ረቡዕ ሌላ ድምጽ ለመስጠት መታቀዱም ተነግሯል፡፡
ድምጹ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው ከትናንት በስቲያ ሰኞ ቢሆንም፣ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች በአዘጋጀችው የውሳኔው ረቂቅ ጽሁፍ ላይ የተደረገው ድርድር ሁለት ጊዜ ወደ ኋላ ተገፍቷል፡፡
ቪኦኤ የተመለከተው ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ፣ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት “በአጠቃላይ በጋዛ ሰርጥ ላሉ የፍልስጤም ሲቪሎች በቀጥታ የሰብዓዊ ዕርዳታው በአፋጣኝ፣ ያለምንም እክል በአስተማማኝ መልኩ እንዲደርስ መፍቀድ፣ ማመቻቸት እና ማስቻልን ይጠይቃል። እንዲሁም ደህንነቱ በተጠበቀ እና ያለንምንም እክል ዕርዳታው እንዲደርስ "ግጭቱ በአስቸኳይ እንዲቆም” የሚጠይቅ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ጽሑፉ በበርካታ የመግቢያ ኬላዎች ወደ ጋዛ የሚገባውን ጭነት የሰብዓዊ ርዳታ መሆኑን ለማረጋገጥ፣ የተባበሩት መንግሥታት የሚከታተልበት ስልት እንዲኖር ያዛል፡፡
እ.ኤ.አ ታህሳስ 8 በጸጥታው ምክር ቤት የሰብዓዊ ተኩስ አቁምን የሚጠይቅ የውሳኔ ሃሳብ ለማጽደቅ የተደረገው ሙከራ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን ተጠቅማ በመቃወሟ መክሸፉ ይታወሳል፡፡
በተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል አምባሳደር ባብ ውድ፣ ከትናንት ማክሰኞ ጧት ጀምሮ ወደ ከሰዓት በኋላ በተገፋው የድምጽ አሰጣጡ ሂደት ላይ “አሁን ድረስ እየሰራንበት ነው” ሲሉ መናገራቸው ተዘግቧል፡፡
መድረክ / ፎረም