በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የእስራኤል የጋዛ ወታደራዊ ዘመቻ ዛሬም ተጠናክሮ ቀጥሏል


የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ ሰርጥ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ እአአ ታኅሣሥ 14/2023
የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ ሰርጥ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ እአአ ታኅሣሥ 14/2023

የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት፣ የሁለት ወታደሮቹንና በመስከረም 26ቱ የሐማስ ጥቃት ወቅት ታግቶ የተወሰደ የአንድ ሲቪል አስከሬንን ማግኘቱን አስታወቀ።

ዩናይትድ ስቴትስ፣ በእስራኤል አጠቃላይ የጦር ዕቅድ ላይ ጫና እያደረገች ባለችበትና ከምታካሒደው ወታደራዊ ጥቃት እንድትታቀብ የሚጠይቀው ዓለም አቀፍ ጥሪ በአየለበት፣ እስራኤል በጋዛ የጀመረችውን ወታደራዊ ዘመቻ አጠናክራ መቀጠሏ ተመልክቷል።

የእስራኤል ጦር ዛሬ እንዳስታወቀው፣ በጋዛ ሼጃያ ወረዳ የነበረውን የሐማስ ወታደራዊ ማዘዣ እና የቁጥጥር ማዕከል አውድሟል። በካን ዮኒስም፣ በሐማስ መሠረተ ልማቶች ላይ “የተነጣጠረ ነው” ያለውን ጥቃት እንደፈጸመም ገልጿል።

ዋሽንግተን በበኩሏ፣ እስራኤል ሐማስን ለማጥፋት የያዘችው ዘመቻ፣ “አካባቢውን ለረጅም ጊዜ እንድትይዝ ወደሚያደርግ አቅጣጫ ማምራት የለበትም፤” ትላለች። ዩናይትድ ስቴትስ እና የአውሮፓ ኅብረት፣ ሐማስን በአሸባሪ ቡድንነት ይፈርጁታል።

በተያያዘ ዜና፣ የዩናይትድ ስቴትሱ ብሔራዊ የደኅንነት ጉዳዮች አማካሪ ጄክ ሱሊቫን፣ ዛሬ ዐርብ፣ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ እና ከመከላከያ ሚኒስትሩ ዮአቭ ጋላንት ጋራ ከተገናኙ በኋላ እንደተናገሩት፣ እስራኤል ጋዛን መልሳ ለረጅም ጊዜ የምትይዝበትን ኹኔታ፣ አገራቸው “ትክክልም ጠቃሚም አይደለም” ብላ እንደምታምን አስታውቀዋል።

በሌላ ዜና፣ አንድ የሄግ ፍርድ ቤት፣ ኔዘርላንድስ፣ የጦር ጀቶች መለዋወጫዎችን ለእስራኤል ለመስጠት ለያዘችው ዕቅድ ይኹንታ ሰጥቷል።

ጉዳዩ ወደ ችሎቱ ያመራው፣ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ቡድኖች፣ የኤፍ-35 የጦር አውሮፕላኖቹ መለዋወጫዎች፣ እስራኤል ከሐማስ ጋራ እያካሔደች ባለችው ጦርነት፣ “ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን በጣሰ መንገድ ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው፤” በሚል ዕቅዱ እንዲሰረዝ ያቀረቡትን ክስ ተከትሎ ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ካለፈው ኅዳር 23 ቀን 2016 ዓ.ም. አንሥቶ፣ በዐሥር ሺሕዎች የሚቆጠሩ ቤት አልባ የጋዛ ነዋሪዎች፣ እጅግ በተጨናነቀና ንጽሕና በጎደለው ኹኔታ በራፋህ እንደሚገኙ፣ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበርያ ቢሮ(UN-OCHA) በዛሬው ዕለት ገልጿል፡፡ ይህም፣ ለበሽታዎች መዛመት አመች ኹኔታ እንዳይፈጥር ስጋት እንዳሳደረበት፣ ኦቻ አክሎ አመልክቷል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG