በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የእስራኤል እና ሐማስ ውጊያ ተባብሶ ቀጥሏል


በደቡባዊ ጋዛ የእስራኤል እና ሐማስ ውጊያ አካባቢው በጭስ ተሞልቷል
በደቡባዊ ጋዛ የእስራኤል እና ሐማስ ውጊያ አካባቢው በጭስ ተሞልቷል

የእስራኤል ኅይሎች ዛሬ ዓርብ በዌስት ባንክ “ቱባስ” በምትባል ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ ስድስት ፍልስጥኤማዊያንን ተኩሰው ገደሉ፡፡

የደቡባዊ ጋዛው የእስራኤል እና ሐማስ ውጊያ ሶስተኛ ወሩን ይዟል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል የጦር ኅይል ባለፈው እ አ አ ጥቅምት 13 ቀን ደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ ስለሞተው የሮይተርስ ጋዜጠኛ ጉዳይ በተያዘው ምርመራ መልስ ሰጥቷል፡፡

የእስራኤል የጦር ኅይል ጋዜጠኛውን ኢሳም አብደላን ስም ሳይጠቅስ ባወጣው መግለጫ “በወቅቱ የሊባኖስ ሄዝቦላ ኅይሎች ድንበር ተሻጋሪ ጥቃት ሲያደርሱ ታጣቂዎቹ ድንበሩን ጥሰው እንዳይገቡ ለመከላከል የአስራኤል ኅይሎች ተኩስ ከፍተዋል” ማለቱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

የእስራኤል መግለጫው አክሎም “ውጊያ ይካሄድበት በነበረው በዚያ አካባቢ የነበሩ ጋዜጠኞች መገደላቸውን ሰምተናል፡፡ ጉዳዩን በመመርመር ላይ ነን”ብሏል፡፡

በተያያዘ ዜና እስራኤል ትናንት ሐሙስ በትላልቆቹ ጋዛ ሰርጥ ከተሞች በሐማስ ታጣቂዎች ላይ ባካሄደችው ጥቃት 350 ሰዎች ተገድለዋል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጥኤማውያን ሲቪሎች ከውጊያው የሚያመልጡበት መጠለያ ፍለጋ ላይ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡

በውጊያው የተፈናቀሉ በርካታ የጋዛ ነዋሪዎች ግብጽ ድንበር ላይ ወደምትገኘው ራፋህ ከተማ ጎርፈዋል፡፡ እስራኤል ፍልስጥኤማውያኑ በውጊያው እንዳይጎዱ ወደተጠቀሰችው ከተማ እንዲሸሹ በራሪ ወረቀቶች በመበተን ማስጠንቀቋ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ሐማስ የሚቆጣጠረው የጤና ሚኒስቴር በሰጠው ቃል ሌሊቱን እስራኤል ባደረሰችው የአየር ድብደባ ቢያንስ 37 መገደላቸውን ገልጿል፡፡

በተያያዘ የእስራኤል የጦር ኅይል ባወጣው መግለጫ የሐማስ ታጣቂዎች ራፋህ ከተማ ከሚገኘው የሰብዐዊ ረድዔት ቀጣና አቅራቢያ ሮኬት ተኩሰዋል ሲል ወንጅሏል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ ጋዛ ውስጥ አንድም ቦታ ከጥቃት ማምለጥ አይቻልም ሲል ተናግሯል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ አዘውትረው ሥራ ላይ በማያውሉት ስልጣን ተጠቅመው የጸጥታ ምክር ቤቱን ሜድቴራኒያን ባህር ዳርቻ ላይ በሚገኘው ስፍራ “እጅግ የከበደ ሰብዐዊ ቀውስ እየመጣ ነው “ በማለት አስጠንቅቀዋል፡፡ የምክር ቤቱ አባላት ተኩስ እንዲቆም እንዲጠይቁም ጉቴሬዥ አሳስበዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር አንተኒ ብሊንከን በበኩላቸው ከብሪታኒያ አቻቸው ዴቪድ ካምረን ጋር ዋሽንግተን ላይ ከተነጋገሩ በኋላ ባደረጉት ጋዜጣዊ ጉባዔ “እስራኤል ሲቪሎችን ከጥቃት እንዲጠበቁ እና ሰብዐዊ ረድዔት በይበልጥ እንዲችል የተቻላትን ሁሉ የማድረግ ግዴታዋን ትልቅ ትኩረት ልትሰጠው ይገባል “ብለዋል፡፡ “እስራኤል ሲቪሎችን ለመጠበቅ ያላት ፍላጎት እና መሬቱ ላይ የሚታየው የተለያየ ነው” ብለዋል ብሊንከን፡፡

በሌላ በኩል አንድ የኋይት ሐውስ ባለስልጣን እስራኤል ህዝብ የሚበዛበት የደቡባዊ ጋዛ አካባቢ ጥቃት ለማካሄድ ያደረገችውን ውሳኔ ደግፈው ተናግረዋል፡፡ የኋይት ሐውስ ምክትል የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪው ጆን ፋይነር ይህን ያሉት ዋሽንግተን ውስጥ በተካሄደው የአስፐን የጸጥታ ጉባኤ ላይ ነው፡፡ አያይዘውም “አሁንም በደቡብ ጋዛ ብዛት ያላቸው ወታደራዊ ዒላማዎች እስራኤል እንዳለችውም አብዛኞቹ የሐማስ መሪዎች አሁንም አሉ ብለን እናምናለን” ብለዋል፡፡

እስራኤል ሐማስ ጋዛን እንዳያስተዳድር ለማድረግ ተነስታለች እና ኢላማዎቹን አሳድዳ መምታት መብቷ ነው ሲሉ ባለስልጣኑ አክለዋል፡፡

አጠቃላይ ተኩስ አቁም ይደረግ የሚሉ ጥሪዎች የሚጠቅሙት ሐማስን ነው የሚለውን የኋይት ሐውስ አቋም ደግመው ያሰሙት ባለስልጣኑ “ቢሆንም እስራኤል ለጋዛ ተጨማሪ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲገባ እንድትፈቅድ ግፊት ማድረጋችንን እንቀጥላለን” ብለዋል፡፡

በአስፐን የጸጥታ ጉባዔው ላይ ንግግር ያሰሙት የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ አገራቸውም ተጨማሪ ሰብዐዊ እርዳታ ጋዛ እንዲገባ ግፊት ማድረጓን ተናግረዋል፡፡ግብጽ እርዳታ እንዳይደርስ ፈጽሞ አልከለከለችም ሲሉም አክለዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG