በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የእስራኤል ጦር፣ በጋዛ 7 የርዳታ ሠራተኞች የተገደሉበት የአየር ጥቃት 'ትልቅ ስህተት' ነው አለ


አንድ ፍልስጤማዊ በእስራኤል የአየር ጥቃት የውጭ ዜጎችን ጨምሮ “ዎርልድ ሴንትራል ኪችን” (WCK ) የተባለው ድርጅት ሰራተኞች የተገደሉበትን ተሽከርካሪ እየተመለከተ በዲር አል በላህ፣ ማዕከላዊ ጋዛ እአአ ሚያዚያ 2/2024
አንድ ፍልስጤማዊ በእስራኤል የአየር ጥቃት የውጭ ዜጎችን ጨምሮ “ዎርልድ ሴንትራል ኪችን” (WCK ) የተባለው ድርጅት ሰራተኞች የተገደሉበትን ተሽከርካሪ እየተመለከተ በዲር አል በላህ፣ ማዕከላዊ ጋዛ እአአ ሚያዚያ 2/2024

የእስራኤል የጦር ኃይል “ጋዛ ውስጥ ሰባት የርዳታ ሠራተኞችን የገደለው የአየር ድብደባ “ከባድ ስህተት ነው” ሲል ዛሬ ረቡዕ በሰጠው መግለጫ ተናገረ፡፡

የእስራኤል የጦር ሠራዊት አዛዥ ሌተና ጄኔራል ሄርዚ ሃሌቪ “ዎርልድ ሴንትራል ኪችን” የተሰኘው የረድዔት ቡድን አባላት የተገደሉበት ጥቃት “በሌሊት ማንነት መለየት ላይ በተፈጠረ ስህተት እና በጣም ውስብስብ በሆኑ የጦርነት ሁኔታዎች ውስጥ የተፈጠረ ክስተት ነው” ብለዋል ።

ሃሌቪ በቪዲዮ በሰጡት መግለጫቸው “ዎርልድ ሴንትራል ኪችን” (WCK ) የተባለው ድርጅት እስራኤልን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ጥሩ ነገር የሚሰራ ድርጅት ነው።” ብለዋል፡

“የእስራኤል ጦር ኃይሎች ከዎርልድ ሴንትራል ኪችን ጋር በቅርበት ይሰራል የሚሠሩትንም ጠቃሚ ሥራ በጣም ያደንቃል” ሲሉም ጀኔራሉ አክለዋል፡፡

የዎርልድ ሴንትራል ኪችን መስራች ሆዜ አንድሬስ ዛሬ ረቡዕ ኒው ዮርክ ታይምስ ላይ በወጣ ጽሁፋቸው እስራኤል "እንቅስቃሴያቸው በመከላከያ ሰራዊቷ በሚታወቅና ግልጽ ምልክት በተደረገባቸው ተሽከርካሪዎች ላይ ቀጥተኛ ጥቃት አድርሳለች" ብለዋል።

ሆዜ አንድሬስ “ጥቃቱ የሰብአዊ እርዳታ ስራን ተስፋ ወደሚያስቆርጥ ደረጃ እንዲያሽቆለቁል ያደረገው ፖሊሲ ውጤት ነው” ሲሉ፣ በእስራኤል ሀማስ ጦርነት ከፍተኛ እርዳታ ለሚሹ ፍልስጤማውያን ርዳታ ለማድረስ ወደ ጋዛ ለመግባት የተቸገሩ የሰብዓዊ ድርጅቶችን ቅሬታ በማጣቀስ ተናግረዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ትናንት ማክሰኞ አመሻሹ ላይ ባወጡት መግለጫ ጥቃቱ “እጅግ እንዳስቆጣቸው እና ልባቸው እንደተሰበረ” ገልጸዋል፡፡

"በጦርነት መካከል ለተራቡ ሰላማዊ ዜጎች ምግብ እየሰጡ ነበር፡፡ ደፋሮችና እና ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆኑ ነበሩ፣ መሞታቸው ያሳዝናል" ሲሉ ባይደን አክለዋል፡፡

“ይህ ጥቃት የአንድ ጊዜ የተለየ ክስተት አይደለም” ያሉት የዩናይትድ ስቴትሱ መሪ “እስራኤል እጅግ ለተቸገሩ ሲቪሎች እርዳታ ማድረስ የሚሞክሩ የርዳታ ሠራተኞችን ደህንነት ለመጠበቅ በቂ ጥረት አላደረገችም” ብለዋል፡፡

ዎርልድ ሴንትራል ኪችን ጥቃቱን ተከትሎ በዚያ የሚያካሂደውን የእርዳታ ሥራ ማቋረጡን ተናግሯል፡፡ ጥቃቱ የደረሰው 100 ቶን የምግብ እርዳታ ዴር አል ባላ የሚገኝ መጋዘን አድርሶ ግቢውን ለቅቆ እንደወጣ መሆኑን ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG