በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

እስራኤል በአየር ሊባኖስን ደበደበች


ደቡብ ሊባኖስ ድንበር ቢንት ጀቤይል በቦምብ ጥቃቱ ወቅት እአአ የካቲት 28/2024
ደቡብ ሊባኖስ ድንበር ቢንት ጀቤይል በቦምብ ጥቃቱ ወቅት እአአ የካቲት 28/2024

እስራኤል ዛሬ ረቡዕ በደቡባዊ ሊባኖስ የሄዝቦላህ የጦር መሣሪያዎች ያሉባቸው ሥፍራዎች ላይ ያነጣጠረ የአየር ድብደባ ማድረሷን አስታወቀች፡፡ ከሊባኖስ ወደ እስራኤል የተተኮሱ በርካታ ሮኬቶችን ማክሸፏንም ተናግራለች፡፡
የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ጋዛ ካን ዮኒስ አካባቢ አዲስ የአየር ድብደባ ማካሄዱን እና በአካባቢው እና በሰሜናዊ ጋዛ ውስጥ በየብስም ወታደራዊ ዘመቻ መፈጸሙንም አስታውቋል።
በሃማስ የሚመራው የጋዛ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ በእስራኤል ጥቃት ቢያንስ 76 ተጨማሪ ሰዎች መሞታቸውን ዛሬ ረቡዕ አመልክቷል።
ጦርነቱ ከጀመረበት እአአ ከጥቅምት ወር አንስቶ ቢያንስ 29 ሺሕ 954 ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች 70,325 ሰዎች ቆስለዋል።
ከሃማስ ታጣቂዎች ጋር ለአምስት ወራት የዘለቀው የእስራኤል ጦርነት በቅርቡ የተኩስ አቁም እና ታጋቾችን የመልቀቅ አዲስ ስምምነት ሊደረስበት እንደሚችል የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን የተናገሩትን ትናንት ማክሰኞ እስራኤል፣ ሃማስ እና የካታር ሸምጋዮች ሁሉም አጣጥለውታል።
እስራኤል ባለፈው ሳምንት ከአደራዳሪዎቹ ጋር በፓሪስ ባደረገችው ንግግር በራማዳን የጾም ወቅት ለአርባ ቀናት ተኩስ እንዲቆም የቀረበውን የተኩስ አቁም ሐሳብ የተቀበለች ሲሆን ሃማስ በበኩሉ የቀረበውን ሓሳብ በማጤን ላይ መሆኑን አመልክቷል፡፡
ሁለቱም ወገኖች በዝርዝር ጉዳዮች ላይ የሚነጋገር የልዑካን ቡድን ካታር ውስጥ ቢኖራቸውም “ለስምምነቱ መሰናክል በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሊያስማማ የሚያስችል የመጨረሻ ስምምነት የለንም፡፡ አንድ ስምምነት እንደምናይ ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ የካታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማጅድ አል አንሷሪ ተናግረዋል፡፡
አንድ የሃማስ ባለስልጣን ለሮይተርስ በሰጡት ቃል "አሁንም መሟላት ያለባቸው ትልቅ ክፍተቶች አሉ። ዋነኞቹ የተኩስ አቁም እና የእስራኤል ጦር የመውጣት ጉዳዮች በግልፅ አልተቀመጡም ይህም ስምምነቱን ያዘገየዋል" ማለታቸው ተጠቅሷል።
“የሀማስ ጥያቄዎች ከእውነታው ውጭ ናቸው” ያሉት የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ታል ሃይንሪች ለስምምነቱ “እኛ ፈቃደኞች ነን፡፡ አሁንም ጥያቄው ሀማስ ፈቃደኛ ነው ወይ?” የሚል ነው ብለዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG