በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ዛሬ ሐሙስ ይጀመራል ተብሎ የነበረው የአራት ቀናት ተኩስ አቁም፣ እንዲሁም በሐማስ የተያዙት ታጋቾች ነጻ መውጣት እና በእስራኤል የታሠሩ ፍልስጢማዊያን መለቀቅ፣ እስከ ነገ ዓርብ መራዘሙ ተነግሯል።
ስምምነቱ ከአየር እና ከምድር የእስራኤል ድብደባ ለሣምንታት ሲደርስባቸው ለነበሩ 2.3 ሚሊዮን ፍልስጤማውያን እፎይታ እንደሚሰጥና፣ የቤተሰብ አባሎቻቸው በሐማስ ለታገቱ እስራኤላውያን ተስፋን የሚሰጥ ነው ተብሏል።
የእስራኤል ብሔራዊ የጸጥታ አማካሪ፣ የስምምነቱ ተግባራዊ መሆን ለዓርብ መተላለፉን ትናንት ማምሻውን ሲያስታውቁ፣ የኳታሩ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በበኩላቸው፣ አደራዳሪዎች አሁንም ስምምነቱ የሚፈጸምበትን አመቺ ሁኔታ በተመለከተ በመሥራት ላይ እንደሆኑ አመልክተዋል።
በሐማስ በምትተዳደረው ጋዛ የሚገኘው የጤና ሚኒስቴር በበኩሉ፣ በጦርነቱ እስከ አሁን ከ13 ሺሕ 300 በላይ ሰዎች እንደተገደሉ አስታውቋል። ቁጥሩ፤ ግንኙነትና አገልግሎት ከተቋረጠባቸውና በሰሜን ጋዛ ካሉ ሆስፒታሎች የሚገኘውን መረጃ እንደማይጨምር ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
በተጨማሪም ስድስት ሺሕ የሚሆኑ ሰዎች እስአ አሁን ያሉበት እንደማይታወቅ እና ምናልባትም በፍርስራሽ ሥር ተቀብረው ሊሆን እንደሚችል ሚኒስቴሩ ስጋቱን ገልጿል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ነታንያሁ በበኩላቸው፣ ግዜያዊው ስምምነት ጦርነቱን እንደማያቆመውና፣ ሐማስ ጋዛን ማስተዳደሩ እስከሚያከትም እና ወታደረዊ አቅሙ ሙሉ ለሙሉ እስከሚደመሰስ ድረስ እንደሚቀጥል ዝተዋል።
መድረክ / ፎረም