በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

እስራኤል በደቡብ ጋዛ ጥቃቷን በማስፋፋት ላይ መሆኗ ተገለጠ


የእስራኤልን የምድር ጥቃት ሸሽተው እየወጡ ያሉ ፍልስጤማውያን እአአ ኅዳር 5/2023
የእስራኤልን የምድር ጥቃት ሸሽተው እየወጡ ያሉ ፍልስጤማውያን እአአ ኅዳር 5/2023

የእስራኤል ኃይሎች በዛሬው ዕለት ከሐማስ ታጣቂዎች ጋር የሚያካሂዱትን ውጊያ ትኩረታቸውን ደቡባዊ ጋዛ ላይ አድርገው ቀጥለዋል፡፡

ውጊያው የቀጠለው ዐለም አቀፋዊ የረድዔት ተቋማት ሲቪሎች ጉዳት ሳያገኛቸው ግጭቱን ሸሽተው መውጫ መንገድ እንደሌላቸው በማሳሰብ ላይ ባሉበት በዚህ ወቅት ነው፡፡

የእስራኤል ታንኮች እና ወታደሮች በደቡባዊ ጋዛ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ወደሆነችው ወደ ኻን ዩኒስ የተጠጉ ሲሆን የአየር ኃይሎቿም በደቡባዊ ጋዛ ጥቃት እያደረሱ መሆኑ ተዘግቧል፡፡

የእስራኤል የጦር ሠራዊት ባለፉት ቀናት ባወጣቸው ማስጠንቀቂያዎች የበርካታ የኻን ዩኒስ መንደሮች ነዋሪዎች ራቅ ወዳሉ የደቡብ ጋዛ አካባቢዎች እንዲሄዱ ሲያሳስብ እንደነበር ተመልክቷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጋዛ ውስጥ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ቢሮ ኦቻ ተናግሯል፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት የፍልስጥኤም ስደተኞች ጉዳይ ቢሮ በበኩሉ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ደቡባዊ ጋዛ ውስጥ በሚገኙ ማዕከሎች ውስጥ መጠለላቸውን አስታውቋል፡፡

ጦርነቱ እንደተጀመረ እስራኤል በሐማስ ላይ የከፈተችውን የጥቃት ዘመቻ ጋዛ ከተማን በመሳሰሉት አካባቢዎች ባፋፋመችበት ወቅት በርካታ የሰሜናዊ ጋዛ ነዋሪዎች ወደ ደቡቡ አካባቢ መሸሻቸው ይታወሳል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በእስራኤል የተያዙ የፍልስጥኤም አካባቢዎች የሰብዓዊ ረድዔት አስተባባሪ ሊን ሃስቲንግስ ትናንት ሰኞ ባወጡት መግለጫ ጋዛ ውስጥ ሰብዓዊ ዕርዳታ እንቅስቃሴ ማካሄድ የሚቻልበት ሁኔታ ያለማቋረጥ መጥበቡን ቀጥሏል ብለዋል፡፡ ጋዛ የሚደርሰው ዕርዳታ መጠንም ከሚያስፈልገው እጅግ በጣም ያነሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ትናንት ሰኞ ጋዛን የጎበኙት የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ፕሬዚደንት ሚርያና ስፖልያሪክ በበኩላቸው ፍልስጥኤማዊያኑ ስላሉበት ስቃይ አሳዛኝ ግምገማቸውን ሰጥተዋል፡፡

እስራኤል በበኩሏ ሐማስ ሆስፒታሎች ስር እና በተለያዩ የሲቪሎች አካባቢዎች ሆን ብሎ ይመሽጋል በማለት ትወነጅላለች፡፡ ሲቪሉን ህዝብ በአየር ጥቃቶቿ እንዳይጎዱ ለቅቀው እንዲወጡ የምትሰጠውን ማስጠንቀቂያ ችላ ብለው እንዲቆዩ በመገፋፋት በከለላነት ይጠቀምባቸዋል በማለትም ትከስሳለች፡፡ ሐማስ አስተባብሏል፡፡

እስራኤል የሐማስን የጋዛ አስተዳደር ለማክተም የወታደራዊ ጥቃት ዘመቻዋን የጀመረችው የቡድኑ ታጣቂዎች እ አ አ ጥቅምት 7 ቀን ደቡባዊ እስራኤል ገብተው ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ ሲሆን በጥቃቱ 1200 ሰዎች መገደላቸውን እና 240 የሚሆኑ ሰዎች ታግተው መወሰዳቸውን እስራኤል ተናግራለች፡፡

ከዚያ ወዲህ በተደረገ ልውውጥ 100 የሚሆኑ ሰዎች ለእስራኤል የተሰጡ ሲሆን እስራኤል በበኩሏ ብዙ መቶ ፍልሥጥኤማውያን እስረኞችን ለቅቃለች፡፡

የሐማስ አስተዳደር የጤና ሚንስቴር እንዳመለከተው ጋዛ ውስጥ ቢያንስ 15 ሺህ 890 ሰዎች ተገድለዋል፡፡ ሰባ ከመቶው ሴቶች እና ሕጻናት መሆናቸውን ገልጿል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG