በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ከከባዱ የእስራኤል ዓየር ድብደባ በኋላ በእስራኤል ጦር እና በሂዝቦላ መካከል ግጭቱ ተባብሶ መቀጠሉ ተዘገበ


 ሰዎች ፍንዳታው በደረሰበት ሥፍራ ተሰባስበው
ሰዎች ፍንዳታው በደረሰበት ሥፍራ ተሰባስበው

በኢራን ከሚደገፈው ሄዝቦላ ጋር ለአንድ ዓመት የሚጠጋ ጊዜ የተካሄደው ግጭት፤ በሊባኖስ እና እስራኤል ድንበር አቅራቢያ የእስራኤል ከፍተኛ የአየር ድብደባ ተባብሶ መቀጠሉን ያመለከተው በሊባኖስ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ኃይል ግጭቱ እንዲረግብ ጠየቀ። የእስራኤል ጦር ሰራዊት በበኩሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሂዝቦላ ሮኬት ማስወንጨፊያዎችን መምታቱን ትላንት ሐሙስ አስታውቋል። የትላንቱ ጥቃት ግጭቱ ከጀመረበትካለፈው ጥቅምት ወር አንስቶ ከታየው ሁሉ የበረታ መሆኑን የሊባኖስ የጸጥታ ምንጮች አመልክተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የጋዛውን ጦርነት ተከትሎ በተቀሰቀሰው የሁለቱ ወገኖች ግጭት ‘ካሁን ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ነው’ በተባለ ጥቃት፤ በያዝነው ሳምንት የሂዝቦላ አባላት ይጠቀሙባቸው የነበሩ የጽሁፍ መልዕክት ማስተላለፊያዎች እና በእጅ የሚያዙ መነጋገሪያዎች ፈንድተው 37 ሰዎች ሲገደሉ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ መቁሰላቸው ተዘግቧል። በእጅ የሚያዙት መነጋገሪያ መሳሪዎች ባትሪዎቻቸው በእንግሊዝኛው አጠራር ፒኢቲኤን በመባል የሚታወቅ ከፍተኛ ተቀጣጣይ ፈንጂ ቅመም በውስጡ የያዙ መሆናቸውን ስለ ጉዳዩ የሚያውቁ የሊባኖስ ምንጮች ለሮይተርስ ገልጠዋል። ፈንጂው በባትሪ ኬሚካል ውስጥ የተዋሃደበት መንገድ መኖሩን ለማወቅ እጅግ አዳጋች ማድረጉንም እነኚሁ ምንጮች አክለው አስረድተዋል።

ደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኘው የመንግስታቱ ድርጅት፤ የሊባኖስ ጊዜያዊ የሰላም አስከባሪ ኃይል፡ ዛሬ ማለዳ ላይ እንዳስታወቀው፤ ባለፉት 12 ሰአታት ውስጥ የሰላም አስከባሪው ኃይል የሚንቀሳቀስባቸውን አካባቢዎች ጨምሮ በሊባኖስ እና በእስራኤል ድንበር አካባቢ ግጭቱ ተባብሶ ቀጥሏል። የድርጅቱ ቃል አቀባይ አንድሪያ ቴኔንቲ ለሮይተርስ በሰጡት አስተያየት፤ ‘የሊባኖስን እና የእስራኤልን ድንበሮች ከሚለየው መስመር አካባቢ የሚታየው ግጭት መባባስ ያሳስበናል። በመሆኑም ሁሉም ወገኖች በፍጥነት ግጭቶቹን እንዲያረግቡ እናሳስባለን” ብለዋል።

የሊባኖስ የጸጥታ ምንጮች በበኩላቸው እንዳመለከቱት፤ እስራኤል በዛሬው ዕለት በፈጸመችው የአየር ድብደባ፤ ደቡብ ሊባኖስ ውስጥ የሚገኙ ሶስት መንደሮች ተመተዋል። የሂዝቦላው አል-መናር ቴሌቭዥን ‘ከጥቃቶቹ በአንዱ የደረሰ ነው’ ሲል ባቀረበው ዘገባ የጭስ ደመና የሚስተዋልበት የቪዲዮ ምስል አሳይቷል።

ይሁንና ከእስራኤል ጦር በኩል ድንገቱን አስመልክቶ እስካሁን የተሰጠ አስተያየት የለም።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG