በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሁለተኛ ሳምንቱን የያዘው የእስራኤል እና የፍልስጤም ግጭት


እስራኤል ጋዛ ላይ የአየር ጥቃት አድርሳለች።
እስራኤል ጋዛ ላይ የአየር ጥቃት አድርሳለች።

ሁለተኛ ሳምንቱን በያዘው የእስራኤል እና የፍልስጤም ግጭት እስራኤል ዛሬ ሰኞ ማለዳ ጋዛ ላይ የአየር ጥቃት አድርሳለች።

የእስራኤል ወታደራዊ አዛዦች እንዳሉት የዛሬ ድብደባ ዒላማ ያደረገው ጋዛን የሚያስተዳድረው ሃማስ የሚጠቀምባቸውን መሹዋለኪያዎች እና የቡድኑን የተዋጊ አዛዦች መኖሪያ ቤቶች መሆኑን ገልጸዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ሃማስ እና ሌሎችም ታጣቂ ቡድኖች እስራኤል ላይ የሚያደርሱትን የሮኬት ጥቃት በአስቸኳይ እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርበው፤ እስራኤልም ብትሆን ራሷን ከጥቃት የመከላከል መብት ያላት ቢሆንም ሲቪሎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የመጠንቀቅ ሃላፊነትም አለባት ብለዋል።

ትናንት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጋዛ ላይ ህይወት እያጠፋ ያለውን የአየር ጥቃት ባፋጣኝ የማቆም እቅድ የለንም ሲሉ ተናግረዋል። ትናንት የእስራኤል ተዋጊ ጀቶች ጋዛ ውስጥ ሦስት ህንጻዎችን በቦምብ አውድመው ቢያንስ አርባ ሁለት ሰዎች ገድለዋል። በአንድ የአየር ጥቃት በተገደሉ ሰዎች ብዛት የትናንቱ ከፍተኛው መሆኑ ታውቋል። ሃማስ ትናንት ዕሁድ ጠዋት ጋዛ ውስጥ ከሚገኝ የሲቪሎች መኖሪያ አካባቢ እስራኤል ላይ ሮኬቶች የተኮሰ ሲሆን አንደኛው ሮኬት ደቡባዊ እስራኤል አሽኬሎን ከተማ የሚገኝ ምኩራብ መትቷል። በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት አልነበረም።

ትናንት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ከፖለቲካ ተቀናቃኛቸው ቤኒ ጋትዝ ጋር የአቋም አንድነታቸውን ለማሳየት ጎን ለጎን ቆመው ለህዝቡ ባደረጉት ንግግር በሙሉ ሃይላችን ማጥቃታችንን ቀጥለናል፣ ጊዜ ይወስዳል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ለዩናይትድ ስቴትሱ ሲቢኤስ ቴሌቭዥን በሰጡት ቃል ጥቃቱ ረጅም ጊዜ እንደማይወስድ ተስፋ አለኝ ብለዋል። ሆኖም ሁለቱ ወገኖች ተኩስ እንዲያቆሙ ለመሸምገል ዓለም አቀፍ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ኔታንያሁ ጥቃቱ ባፋጣኝ የማቆም ዕቅድ የለንም ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ትናንት ሊባኖስ ውስጥ በመቶዎች የተቆጠሩ ሰዎች እስራኤል ጋዛ ላይ የምታደርሰውን ጥቃት በመቃወም ሰልፍ አካሂደዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት ግጭቱን ለመብረድ ስለሚቻልበት መንገድ ትናንት ስብሰባ አድርጎ የተነጋገረ ሲሆን ዩናይትድ ስቴትስ በበኩሏ ሁለቱ ወገኖች ተኩስ ለማቆም እንዲስማሙ የሚሞክሩ ዲፕሎማት ልካለች። ፕሬዚደንት ጆ ባይደን የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁን እንዲሁም የፍልስጤም ፕሬዚደን ማህሙድ አባስን በስልክ አነጋግረዋል።

የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ነገ ማክሰኞ በርቀት በኢንተርኔት ቪዲዮ አማካይነት ተስብስበው እየተባባሰ ስለመጣው ግጭት ይወያያሉ ተብሏል።

XS
SM
MD
LG