በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

እስራኤል በረመዳን በጋዛ የምታካሂደውን ጥቃት ለማቆም ተስማማች


የዩናይትድ ስቴስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በ"ሌት ናይት ዊዝ ስቲቭ ሜየርስ" ፕሮግራም ላይ
የዩናይትድ ስቴስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በ"ሌት ናይት ዊዝ ስቲቭ ሜየርስ" ፕሮግራም ላይ

ከመጋቢት አንድ ጀምሮ ለአንድ ወር በሚቆየው የሙስሊሞች ቅዱስ የረመዳን ወር፣ እስራኤል በጋዛ የምታካሂደውን ወታደራዊ እርምጃ ለማቆም መስማማቷን፣ የዩናይትድ ስቴስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስታወቁ።

ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት ኤንቢሲ በተሰኘው የአሜሪካ ቴሌቭዥን ጣቢያ ከሚተላለፈው "ሌት ናይት ዊዝ ስቲቭ ሜየርስ" የተሰኘ ፕሮግራም ጋር ሰኞ ምሽት ባደረጉት ቆይታ ነው።

እስራኤል ውሳኔውን ያሳለፈችው የአረብ ሀገራት፣ ጦርነቱ በረመዳን ወቅትም የሚቀጥል ከሆነ በቀጠናው ያለውን ውጥረት የበለጠ ሊያባብስ ይችላል የሚል ስጋት ባደረባቸው ወቅት ሲሆን፣ በኳታር ላይ የሚካሄደው የተኩስ አቁም ድርድርም ተጠናቅሮ ቀጥሏል።

በቃለ መጠይቁ ወቅት፣ ባይደን በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት በመርህ ደረጃ መደረሱን እና በሚቀጥለው ሳምንት ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችልም ገልጸዋል።

በጋዛ የሚካሄደው ጥቃት መቆሙ፣ በጥቅምት ሰባት የተያዙት ቀሪዎቹ የሐማስ ታጋቾች እንዲፈቱ ጊዜ እንደሚሰጥም ተናግረዋል። ሐማስ በደቡብ እስራኤል ባደረሰው ጥቃት ከ250 በላይ ታጋቾችን የወሰደ ሲሆን ከ1ሺህ 200 በላይ ደግሞ ተገድለዋል። እስራኤል በምላሹ ጋዛ ላይ ባካሄደችው ጥቃት፣ ከ30 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን የጋዛ ጤና ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

ባይደን አክለው እስራኤል ከቀሪው ዓለም ድጋፍ ልታጣ ትችላለች ያሉ ሲሆን፣ እስራኤል "ቀሪ" የሐማስ ዒላማ ያለቻቸው ላይ ጥቃት ማድረስ ከመቀጠሏ በፊት፣ በሚሊየን የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በጦርነት የተተራመሰውን የጋዛ አካባቢ ሸሽተው ከተጠለሉበት የራፋ ከተማ ለማስወጣት ቃል መግባቷን ተናግረዋል።

ጦርነቱን ለማቆም የመጨረሻው ስምምነት የተደረገው በህዳር ወር ሐማስ ከ100 በላይ ታጋቾችን በለቀቀበት ወቅት ሲሆን፣ እስራኤል በምትኩ ሦስት እጥፍ የሚሆኑ ፍልስጤማዊ እስረኞችን ለቃ ነበር።

እስራኤል ግን ሐማስ እስካልጠፋ ድረስ አሁንም ጦርነቱን እንደማታቆም መናገሯን የቀጠለች ሲሆን ሐማስ በበኩሉ ጦርነቱን ለማቆም ስምምነት እስካልተደረሰ ድረስ ታጋቾችን እንደማይለቅ አስታውቋል።

በመጪው ህዳር ወር ለሚደረገው ምርጫ በድጋሚ ለመመረጥ ዝግጅት እያደረጉ ያሉት ባይደን፣ ለእስራኤል ባሳዩት ጠንካራ ድጋፍ እና በጋዛ በደረሰው ከፍተኛ የሞት ቁጥር ምክንያት፣ በወጣት አሜሪካውያን እና ግራ ዘመም ተራማጆች ዘንድ የነበራቸው ድጋፍ አሽቆልቁሏል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG