የእስራኤል እና የሐማስ ውጊያ በሆስፒታሎች አካባቢም ጭምር በቀጠለበት ሁኔታ፣ በሺሕ የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ዛሬ ሰኞ ሰሜን ጋዛን ለቀው ወጥተዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዲሬክተር የሆኑት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በበኩላቸው በጋዛ ትልቁ የሆነው ሺፋ ሆስፒታል፣ እንደ ሆስፒታል ማገልገል ማቆሙን አስታውቀዋል። በሆስፒታሉ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ እና አደገኛ መሆኑንም ገልጸዋል።
የሆስፒታሉ ጄኔሬተር ነዳጅ በመጨረሱ አራት ታካሚዎች እና ከግዜው ቀድሞ የተወለደ ሕፃን ሕይወታቸውን እንዳጡ ተዘግቧል።
በሆስፒታሉ አካባቢ ያለው ተኩስ እና የቦምብ ፍንዳታ ቀድሞውንም ያለውን አስከፊ ሁኔታ እንዳባባሰው ዶ/ር ቴድሮስ ጨምረው ገልጸዋል።
የሐማስ ኃይሎች በሆስፒታሉ ውስጥ እና በአካባቢው ከሚገኙ ሲቪሎች መሃል በመደበቅ እንደ ማዘዣ ጣቢያም ይጠቀሙበታል ስትል እስራኤል ትከሳለች፡፡ እስራኤል ለክሷ የፎቶም ይሁን የቪዲዮ ማስረጃ እንዳላቀረበች ተዘግቧል። የሐማስ ተጣቂዎች በመኖሪያ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ እና በት/ቤት እና መስጊዶች አካባቢ ደግሞ ሮኬት እና ሌሎችንም መሣሪያዎች ሲያዘጋጁ የሚያሳይ ምስል እስራኤል ከዚህ ቀደም ይፋ አድርጋ ነበር።
አል ቁድስ የተባለ ሌላ ሆስፒታል ነዳጅ በማጣቱ ምክንያት ትናንት እሁድ መዘጋቱም ታውቋል። 6ሺሕ የሚሆኑ ታካሚዎችን እና ሠራተኞችን የእስራኤል ጦር እንዲያሰወጣ ለማድረግ ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑን ሆስፒታሉን የሚያስተዳድረው የፍልስጤማውያን ቀይ ጨረቃ ማኅበር አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ነታንያሁ በበኩላቸው 100 የሚሆኑ ታካሚዎችን ከሺፋ ሆስፒታል ማስወጣት መቻሉን እና በአካባቢው ይገኙ የነበሩ በአስር ሺሕዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንም እንዲለቁ መደረጉን ትናንት ከሲኤኔኤን ቴሌዝዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።
መድረክ / ፎረም