በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የነዳጅ እጥረትና የስልክ መቋረጥ የጋዛውን እርዳታ አወሳስቦታል


እስራኤል እና ፍልስጤም ግጭት በቀጠለበት ፍልስጤማውያን ከዳቦ ቤት ዳቦ ለመግዛት ወረፋ ሲጠባበቁ፣ ደቡባዊ ጋዛ ካን ዮኒስ፣
እስራኤል እና ፍልስጤም ግጭት በቀጠለበት ፍልስጤማውያን ከዳቦ ቤት ዳቦ ለመግዛት ወረፋ ሲጠባበቁ፣ ደቡባዊ ጋዛ ካን ዮኒስ፣

ጋዛ ውስጥ ከነዳጅ መጥፋት እስከ ስልክ አለመሥራትና የመኪና እጦት የተንሠራፋው ችግር እርዳታ የማቅረቡን ሥራ እያወሳሰበው መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣናት ዛሬ (ዓርብ) ተናገሩ።

የአካባቢው ሁኔታ ፈጥኖ ወደ ከፋ ቸነፈርነት ሊለወጥ እንደሚችል የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ሲንዲ መኬን ትናንት አስጠንቅቀው ነበር።

ጋዛ ውስጥ የምግብና የውኃ አቅርቦት እንደሌለ መኬን ጠቁመው ከሚያስፈልገው እርዳታ እየገባ ያለው እጅግ ጥቂቱ መሆኑን ገልፀዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ አያይዘውም “አሁን ያለውን ረሃብ ለማስታገስ የሚችል እርዳታ ለማስገባት አንድ የድንበር ኬላ በቂ አለመሆኑን አመልክተው የደኅንነት ዋስትና ያለው ተጨማሪ መተላለፊያ መሥመር መክፈት አስፈላጊ እንደሆነ አሳስበዋል።

በሌላ በኩል ሺፋ ሆስፒታል ውስጥ ላሉ ህሙማን አራት ሺህ ሊትር ውኃና አንድ ሺህ አምስት መቶ የተዘጋጀ ምግብ ትናንት ማድረሱን የእሥራኤል ጦር አስታውቋል።

እሥራኤል የሃማስ ታጣቂዎች በሆስፒታሉ አቅራቢያ ይጠቀሙባቸዋል ያለቻችውን የምድር ውስጥ መሹለክለኪያ ዋሻዎችን የሚያሳይ ቪዲዮ ትናንት ሐሙስ አውጥታለች።

ሃማስ ትናንትናውኑ ማምሻው ላይ በሰጠው ምላሽ “ግልፅ የውሸት ትርክት መደጋገም ነው” ሲል አጣጥሎታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁም በእሥራኤላዊያን ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሰላማዊ ዜጎችን ጉዳት በመቀነስ በኩል ፈተናዎች እንዳሉ አመልክተዋል።

እሥራኤል ሰላማዊ ሰዎች ደቡባዊ ጋዛን ለቅቀው እንዲወጡ አዲስ ትዕዛዝ ያስተላለፈች ሲሆን ይህም ወታደራዊ እርምጃው ሊስፋፋ እንደሚችል የሚጠቁም ፍንጭ መሆኑ ተመልክቷል።

ሃማስ የያዛቸውን ታጋቾች በሙሉ እንዲለቅና ለነፍስ አድን እንቅስቃሴዎች ሲባል የተራዘሙ ተኩስ የማርገብ ፋታዎች እንዲደረጉ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ጠይቋል።

ይሁን እንጂ እሥራኤል የውሣኔ ሃሣቡን ከመሠረቱ እውነታ ጋር ያልተገናኘ ነው ስትል ትተቸዋለች።

በተባባሰው ግጭት ከአንድ ሚሊየን ተኩል በላይ ሰው የተፈናቀለ ሲሆን በጋዛው ቀውስ ሊደርሱ የሚችሉ ተጨማሪ አሳዛኝ ሁኔታዎችን ለመከላከል አስቸኳይ እና የተቀናጀ ዓለምአቀፍ ምላሽ እንደሚያስፈልግ ተመልክቷል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG